20110429
ከሦስት ሺሕ በላይ ኢአማንያን ዳግመኛ ተወለዱ።
በከንባታ ጠንባሮ እና አላባ ሀገረ ስብከት በተካሔደ ሐዋርያዊ ጉዞ ከሦስት ሺሕ ስድስት መቶ በላይ ኢ አማንያን ተጠምቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጅነትን አግኝተዋል። የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፤ የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር በሸፈነው ሙሉ ወጪ የካቲት 19 ቀን 2003 ዓ.ም በተደረገው ሐዋርያዊ ጉዞ በርካታ ምእመናን ቃለ እግዚአብሔርን ከማግኘታቸው በተጨማሪ የሌላ እምነት ተከታዮችም በመጠመቃቸው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል። ጉባኤው በተ ደረገባቸው በዱርጊ መንበረ ሰብሐት ቅድስት ማርያምና በእምብኩና ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ሠላሳ አንድ፤ በሀደሮና ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ በኦጆራ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ አንድ ሺሕ ሦስት መቶ ስልሣ አራት በአጠ ቃላይ ሦስት ሺሕ ስድስት መቶ ዘጠና አምስት የሌላ እምነት ተከታይ የነበሩ በብፁዕ አቡነ ቀለምኒጦስ የከንባታ ሀድያ ስልጢ ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ እጅ ተጠምቀዋል፡፡ |
«የእግዚአብሔር ዓላማ ማንም ሰው የመንግሥቱ ወራሽ እንዲሆን ነው፡፡ ዛሬ የተጠመቃችሁትም የእግዚአ ብሔር ልጆች ሆናችኋል» ያሉት ብፁዕነታቸው፣ «የእግዚአብሔር መንግሥትን ለመውረስ የሚያስችላችሁን መልካም ሥራ መሥራት፣ በጸሎትም መትጋት እና በሃይማኖት መጽናት ያስፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆናችሁ ከማኅበረ መላእክት እና ከቅዱሳኑ ስለተቀላቀላችሁ ደስ ይበላችሁ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሥጋዊውም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወታችሁ ትጸልያለች» ብለዋል፡፡
የከንባታ ጠንባሮ አላባ ሃገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ሚካኤል ገብረ ማርያም በበኩ ላቸው፤ ጥምቀቱን ተቀብለው የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ልጅነትን ያገኙት ምእመናን፣ በክርስቲያናዊ ሕይወታቸው መጠንከር፣ በጸሎት መትጋትና መማር እንዳለባቸው አሳስበው ወደፊ ትም፤ «እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው ባላቸው ሙያ ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማገልገል እና በእርሷም የመገልገል መብት አላቸው» ብለዋል፡፡
«በዛሬው ዕለት የተጠመቃችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ከጨለማ ወደ ብርሃን ዘለዓለማዊ ሕይወት ተሸጋግራችኋል፡፡ ስለዚህ መንግሥተ እግዚአብሔርን የሚያስገኝ በጎ ሥራ እንድትሠሩ በጾም በጸሎት ትጉ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለእናንተ የሚገባችሁን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነች» ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ሀገረ ስብከቱ ሕዝቡን በትጋት ለማገልገል ቃል መግባቱን ተናግረዋል፡፡
/ ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ሚያዝያ 1-15 2003 ዓ.ም /
20110215
ወለንኪ ቅዱስ ዮሓንስ ወቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በቃጠሎ ሙሉ ለሙሉ ስለመዉደሙ

ባለፈው አመት ጥር 2002 ዓ.ም ከ አስገራሚው እና ታሪክን በ ሰሩ ወጣቶች ተከብሮ ከዋለው የ ጥምቀት በዓል በኃላ የተሰማው አስደንጋጭና አሳዛኝ ዜና ነበር:: እሱም በምዕራብ ሽዋ ከ አዲስ አበባ 65 ኬ.ሜ እርቆ የሚገኘው የ ወለንኪ ቅዱስ ዮሓንስ ወቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ባልታወቁ ወገኖች ሙሉ ለሙሉ መቃጠል ነበር:: በቃጠሎው ከታቦቱ በስተቀር መላው ቤተ ክርስቲያኑና ንዋየ ቅዱሳት ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል::ይህም ድርጊት በከተማዋና በዙሪያዋ ብሎም በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የተዋህዶ ልጆች እና ሀገራቸዉን የሚወዱ ወገኖችን ያስቆጣ ነበር እኩይ ተግባር ነበር:: በአጭር ጊዜ ዉስጥ ቤተክርስቲያኑ ተሰርቶ ንዋያተ ቅዱሳት ተማልቶ አገልግሎት መስጠት ጀምራል::አሁን ግን ያ ሁሉ አልፎ ቤተክርስቲያንዋ እንደገና አገልግሎት መስጠት ጀምራለች ሁሉን ያከናወነልን እግዚአብሔር ይመስገን:: "የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።" ማቴ 16:18 ግራኝ አህመድም ዮዲት ጉዲት ሁሉም ተዋህዶን ለማጥፋት ሞከሩ አልቻልሙም ይልቁንስ እየሞትን በዛን በመግደል ጽድቅ እንደሌለ በ እርግጥ አሳይተናል ለምሳሌ ፓዉሎስ አንገቱን ተሰየፈ ጴጥሮስም ተሰቀለ ብዙ ቅዱሳን በ ስቃይ እንዳለፉም እናዉቃለን የተዋህዶ ልጆች ዛሬም በ ስቃይ በፈተና ማለፍን ከ አባቶቻችን ተምረናል እና ቀዳሚ በሆነችው ተዋህዶ እንጽና ፍቅርን ያስተማረን የ እግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው እና ክፉን አትፍሩ
20110201
ጻድቁ አባታቺን አቡነ ተክለ ሃይማኖት

አቡነ ተክለኃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ ዓ.ም ታሕሣሥ ፳፬ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ወይም ደስታዋ ማለት ነው፡፡
ወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በአሥራ አምስት ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ /ጌርሎስ/ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ኃሃይማኖት» አለው፡፡ ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡
አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ
«አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡»
/ገድለ ተክለ ኃይማኖት ምዕ ፳፰ ቁ ፪ - ፫
ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ኃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲገልፅ:-
* «እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» /ዕብ. ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ / እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡
* «ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡
* «የአንበሶችን አፍ ዘጉ» ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ /ምዕ ፲፩ ቁ ፴፬ /እንዳለው አባታችንም የአውሬውን ፥ የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጠዋል።
* «ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡
* «ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡
ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁ?» እያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡
በመጨረሻም አባታችን በነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸው ሆነ፡፡ በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችንለእኚህ ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡ እኛንም ከጻድቁ ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
20110115
1. ምስጢረ ሥላሴ

ሥላሴ ማለት የግእዝ አጠራር ነው። ትርጉሙ ሦስትነት ወይም ሥሉስነት ማለት ነው። የምስጢረ ሥላሴ ሁኔታ በዘመነ ብሉይ እንደ አሁኑ /ዘመነ ሐዲስ/ ግልጽ አልነበረም። ይህ ለብዙ ዘመናት ለጥቂቶች ግልጽ ለብዙዎች ግን ሥውር ሆኖ የነበረው ምስጢር ጐልቶ የወጣው በክርስቶስ መገለጥ ወይም ሥጋችንን ለብሶ ወደዚህ ዓለም መምጣት ነው። ጌታ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ በማያሻማ መልኩ ተገልጧል /ማቴ 3፥16/::
ሥላሴ ስንት ናቸው? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ሥላሴ አንድም ሦስትም ይሆናሉ /ናቸው/ የሚል ነው። ይህን መልስ ተከትሎ የሚመጣ ጥያቄም አለ እሱም ''ሥላሴ በምን አንድ ይሆናሉ በምን ሦስት ይሆናሉ'' የሚል ነው። የሁሉም መልስ ቀጥሎ ያለው ነው።
የሥላሴ አንድነት
ስለ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ስናነሳ ቀድመን የምንመለከተው ''አንድነትን'' ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ለአንድነታቸውና ለሦስትነታቸው መቀዳደም ኑሮበት ሳይሆን የቁጥር መሠረት አንድ ስለሆነ በዝያው ለመጀመር ነው /እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ/ ሥላሴ አንድ ይሆናሉ በምን? በዐይነ ሥጋ የማይታይ የሰው አዕምሮ የማይመረምረው፣ የሰው ሕሊና አስሶ የማይደርስበት ከዓለም በፊት የነበረ በማዕከለ ዓለም ያለ፣ ዓለምን ኣሳልፎ የሚኖር አምላክ መኖሩን እናምናለን። እርሱም ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ነው።
በምን አንድ ይሆናል ለሚለውም፦
1. በመለኮት:- መለኮት ማለት "መለከ - ገዛ" ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሆኖ ''ግዛት'' ማለት ነው። በእብራይስጥም ማልኮት ይባላል። እንግዲህ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኮት ይህም ማለት በግዛት በመንግስት አንድ ናቸው። ለዚህም ቅ/መጽሐፍና አበው ተባብረውበታል።
- ''መንግስትህ የዘለዓለም መንግስት ናት ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው::" /መዝ 144፥13/ /መዝ 145፥10/ /መዝ 73፥12/
/ዳን 4፦3/ /ዳን 4፥34/ /1ተስሎ 2፥12/
- "በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና::" /ቈላስ 2፥9/
- የመለኮቱ ኃይል በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰለ ---ሁሉን ስጠን /2ጴጥ1፥3/
እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ''መለኮቱ'' አለ እንጂ ''መለኮቶች'' በማለት አላበዛውም።
አበው ይህን መነሻ በማድረግ ያሉትንም እናስከትላለን::
+ ዮሐንስ ዘእስክንድርያ ''እስመ ምስጢረ ሥላሴ ይትሌለይ በአካላት ወኢይትሌለይ በመለኮት። ወመለኮቶሙስ አሐዱ ውእቱ። አኮ ከመ ዘርሁቃን ይትቃረቡ በበይናቲሆሙ በሱታፌ ተራክቦ አላ እሁዛን በጽምረተ አሐዱ መለኮት" ብሏል።
+ ሚናስ ዘእስክንድርያ:- "መለኮትኒ ይትዐወቅ ከመውእቱ ያኅብር ቅድስተ ሥላሴ።"
+ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ:- "መጻሕፍትሒ ቅዱሳት ያቤይና ከመውእቱ አሐዱ መለኮት'' ካለ በኋላ "ወበዝንቱ አዕመርነ ከመ አሐዱ ውእቱ መለኮት ዘቦቱ ሠለስቱ አካላት'' ብሏል።
+ ዲዮናስዮስ ዘእስክንድርያ:- "ይሤለሱ በአካላት ወይትዋሐዱ በመለኮት ወሶበሂ ንሬሲ ቅድስተ ሥላሴ ፍሉጣነ መለኮት ዘከመ አካላቲሆሙ ንትአመን እምነተ ሰይጣናዌ::'' ብሏል:: ሊቁ በተጨማሪም ''ንህነሰ ከመዝ ንሰግድ ለአሐዱ አምላክ ባሕቲቱ ወንትአመን በአሐዱ መለኮት ዘሠለስቱ አካላት ወኢንበውእ ኅበ ከፊለ መለኮት ወመንግስት'' ሲል አስተምሯል።
እነዚህ ደጋግ አባቶች እግዚአብሔር በመለኮት አንድ መሆኑ በማያሻማ መንገዱ አመስጥረው አስቀምጠውታል።
ርዕሱን ከማጠቃለላችን በፊት ከቤተክርስቲያን አባቶች ውጭ የሆነ ዋርፊልድ የተባለ ፀሓፊ ያለውን እንጥቀስ።
ዋርፊልድ ስለ ቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት የሚከተለውን ጽፏል:: ''መቼም ቢሆን ቃላት ነገረ-እግዚአብሔርን በትክክል ሊገልጹልን አይችሉም። ቢሆንም ግን አንድን ነገር ለማብራራት ሌላ አማራጭ ስለሌለን የትም አንሄድም ''አንድና እውነተኛ አምላክ አለ። ይህም አንድ አምላክ ሦስት እኲል አካላት በመለኮት አንድ የሁኑ በአካል ግን የተለዩ አሉት'' ብሏል። /ዋርፊልድ የቲኦሎጂ ትምህርት ቢኖረውም ዓለማዊ ፀሓፊ ነው።/
ቤተክርስቲያን ትምህርት የተካኑት አባቶቻችን ሃይማኖታቸውን ይህን ይመስላል።
2. በባሕርይ:- ባሕርይ ማለት "ብሕረ ተንጣለለ፥ ሰፋ፥ ዘረጋ" ከሚለው ግስ የወጣ ነው። በቲኦሎጂ /በነገረ መለኮት/ ቋንቋ ሲፈታም ባሕርይ ማለት ሥርው፥ ነቅዕ አዋሃጅ /የሚያዋሕድ/ አስተገባኢ ማለት ነው። ባሕርይ አካል ሥራውን የሚሠራበት መሣሪያ ነው። አባቶች 'አንዳርጌ ሰብሰቤ' እንደማለት ነው ሲሉ "አስተጋባኢ" ብለውታል። ባሕርይና አካል እንደ አጽቅና እንደ ሥር አንድ ናቸው አይለያዩም አንዱ ያለ አንዱ መኖር አይችልም።
+ ባሕርይ ሥር፥ ምንጭ፥ አዋሐጅ የተባው ለምንድን ነው? ቢባል ሥርና ምንጭ ከእርሱ ለሚበቅለውና ለሚመነጨው ወይም ለሚወጣው ነገር ጥንትና መሠረት እንደሆነ ሁሉ ባሕርይም የአካልና የግብር የስምም መሠረት ነውና ሦስቱን አካላት የሚያስገኝና የሚያዋሕድ ስለሆነ ነው። እዚህ ላይ ባሕርይ መሠረት አስገኝ ስለተባለ ባሕርይ ከአካል ከስምና ከግብር ባነጋገር እንጂ በመኖር የሚቀድም ሆኖ አይደለም። ባነጋገር ግን የቁጥር መሠረት አንድ ስለሆነ ነገርን ከስሩ ለማምጣት 3 ከሚሰኙበት ነገር አንድ የሚሰኙበት ነገር መነሻ ማድረግ ስለሚገባ ነው። በዚህ መሠረት ሥላሴ በባሕርይ አንድ የሚሆኑበት ሥረ-ነገር ምንድን ነው? ያልን እንደሆነ:-
- መፍጠር:- ''አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው:: /መዝ 101፥25/ አሁን የተመለከትነው ጥቅስ ''ምድርን መሠረትህ'' ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው አለ እንጂ::
- ምድርን መሠረታችሁ የእጃችሁ ሥራ አላለም።
- ከዚህ በተጨማሪ ሥላሴ በመፍጠር ባሕርያቸው አንድ እንደሆኑ ብዙ መጥቀስ ቢቻልም ጥቂቱን ብቻ እነሆ (ዘፍ 1፥1) (ኢሳ 44፥24) (ኢሳ 40፥22) (ኢሳ 66፥2) (ኤር 10፥12) (ኤር 51፥15)
- ከዚህ በተጨማሪ ሥላሴ በባሕርይ አንድ የሚሆኑባቸው ነገሮች
መስጠት፣ መንሳት፣ መግደል፣ ማዳን ባጠቃላይ ሁሉም ቻይነት፥ ግዛት ጥበብ፥ ዕውቀት ምክር፥ ሥምረት እንዲህ ያለ ስመኛ ቃል ሁሉ የባሕርይ አንድነታቸውን ያሳያል። ይህም በመሆኑ ቅድምናቸውና ዕሪናቸው አንድ ነው። መቅደም መቀዳደም፣ መብለጥ መበላለጥ የለባቸውም። ይህ ሁሉ የሆነው ባሕርያቸው አንድ በመሆኑ ነው፦
ቅ/ቄርሎስ ''ኢይቀድም አሐዱ እምካልዑ : ወካልኡ እምሣልሱ አሐቲ ቅድምናሆሙ ለሥላሴ። ኢሀሎ አብ ዘመነ ዘእንበለ ወልዱ ወመንፈሱ አሐተ ስዓተ-ወኢ ከመ-ቅጽ በተዓይን። ሥላሴ ዕሪት ዘእንበለ ፍልጠት::
3. በኅልውና:- ሕልውና ማለት "ነዋሪነት፥ ኑሮ፥ አነዋወር" ማለት ነው። በነገረ መለኮት ቋንቋ አፈታት ግን አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ኅልው ሆኖ፣ ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ኅልው ሆኖ፣ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ኀልው ሆኖ በመኖር አንድ ናቸው ማለት ነው። በሌላ አባባልም ህልውና ሦስትነታቸውን ሳይጠቀልለው፣ ሦስትነትም አንድነታቸውን ህልውናውን ሳይከፍለው አንዱ ከአንዱ ጋራ ተገናዝቦ ባንድነት መኖር ነው። /በኲነት ርዕሳችን የበለጠ ይብራራል/
- ጌታ ስለ ኅልውናቸው አንድነት የሚከተለውን ብሏል። ''ኢተአምንሁ ከመ አነ በአብ ወአብ ብየ'' /ዮሐ 14፥9-11/
+ ዮሐንስ ዘእስክንድርያ:- "ነአምን እስመ አብ ህልው በወልድ ወበመንፈስ ቅዱስ። ወወልድኒ ኅልው በአብ ወበመንፈስ ቅዱስ፣ ወመንፈስ ቅዱስኒ ህልው በአብ ወበወልድ።" እንዳለ/ የሥላሴ አንድነት እኛ ከምናውቀው ''አንድ'' የተለየ ነው በዚህ አንድነት ውስጥ ሦስትነት አለና ይኸውም የሚከተለው ነው::
. ይቀጥላል
20101016
በ እኛ ነዋየተ ቅዱሳን የመናፍቃን ጭፈራ
የማቴዎስ ወንጌል7፥15
ዛሬ ይህን ለመጻፍ ያስገደደኝ ትላንት አንድ ጋደኛዬ ኢትዮ ትዩብ በሚለው ድህረ ገጽ ላይ የወጣዉን ምስለ ድምጽ ( http://www.ethiotube.net/video/8669/Yetsidiq-Tsehay-Ethiopian-Gospel-Singers%EF%BB%BF ) መናፍቅኑ ከዚህ በፊት በ ቅድስት ቤተክርስትያናችን ላይ ያልሆኑ ስብከቶችን እና የ እኛ የ ሆኑ የዘማ እቃዎችን በመጠቀም ሲዘፍኑ አይተናል በዚም አላበቁም ከ 4 እና 5 አመታት በፊት ዉዳሴማሪያምን ቀየር አድርገዉ ዘመን ባፈራዉ የድምጽ መሳሪያ በመጠቀምን ሲዘፍኑም አይተን አልፈናል የቅርብ ጊዘዉን ላስታዉሳቹ አንድ በልመና የሚተዳደር ሰዉን በገንዘብ ይሁን በሃይ በማስፈራራት አቡነ ያሬድ ነኝ ብሎ የሃሰትምስክርነት እንዲሰጥ ተደገ ይህንንም በዝምታ አለፍን.ለ ኢትዮጲያ ድህነት ተጠያቂዎ የ ኦርቶዶክስ በተክርስትያን ናት ሲሉም አድምጠን አልፈናል
እዚህ ላይ ሳልጠቅስ ማለፍ የማልፈልገዉ ነገር የ መምህር ዘበነን እዉነትን የማዉጣት ስራ ሊበረታታ ይገባዋል . የ ሃይማኖት መሪዎቻችንም በዚህ ነገር ላይ መላ ቢሉ ጥሩ ነው እላለው
ይሄን ቪድዮ ከሌላዉ ለየት የሚያደርገዉ የከበሮዉ፣ የፀናጽሉ፤ የመቋሚያው አላንስ ብሎ መፆረ መስቀሉን፣ጽናውን፣ ቃጭሉን ይዘዉ ሲጨፍሩ አየን ይህንንስ በዝምታ ማለፍ ያለብን አይመስ ለኝም. አባቶቻችን ያቆይልንን የዜማ መሳሪያዎችን እና ንዋያተ ቅዱሳቱን ይዘው ሲጨፍሩ ዝም ካልን የሚቀትለዉ ታቦትን ይዘዉ ይሆናል የሚጨፍሩት.
የቀደሙት አባትኦቻችን ያቆዩልንን ኦርቶዶስ ተዋህዶን እኛም ከ የዜማ መሳሪያዎቻቻን እና ንዋያተ ቅድሳቱ ከሙሉ ሚስጥርና ትርጉማቸው ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፉ የእኛ ሀላፊነት ነው።
ተኩላዉ ለምድ ለብሶ በርግጥ መጣል እና
አምላክ ሆይ አድነን ፍጠን ተሎ ና
20101006
እንኳን ለዘመነ ጽጌ በስላም አደረስን
ስለዚህም ሰብአ ሰገልን አስጠርቶ «ሂዱ ሕፃኑን ፈልጉ ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔም እንድሰግድለት ወደ
እኔ ተመልሳችሁ ያለበትን ንገሩኝ» በማለት በሽንገላ ተናገራቸው፡፡
ጠቢባኑም ከሄሮድስ ከተለዩ በኋላ በኮከቡ እየተመሩ ጉዞአቸውን ቀጥለው ጌታችንን ከእናቱ ጋር አገኙት ፤ ተንበርክከው ሰገዱለት፤ ወርቅ ፣ ዕጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡
የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ ነገር ግን መንገድ ቀይረው ወደ ሀገራቸው እንዲሄዱ በነገራቸው መሠረት በሌላ መንገድ ወደ መጡበት ተደብቀው ተመለሱ፡፡
«እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ «ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነስ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሸ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡ » /ማቴ. 2 13 14/.......ዮሴፍም ተነሣ በዕድሜዋ በጣም ልጅ የነበረችው እመቤታችን ገና የተወለደውን ሕፃን አቅፋ የምትቀመጥበት አህያም ተዘጋጀ፡፡
ጉዞአቸውን ጀመሩ........
በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ዘመነ ጽጌ ወርኃ ጽጌ ይባላል:: ይኸውም ተራሮችን ሸንተረሮችን በአበባ ያስጌጠ ሰማይን በከዋክብት ያጌጠ ምድርን በስነ ጽጌያት ያሸበረቀ አምላክ ነው እና:: እሱ የሚመሰገንበት ስለሆነ .....ሌላው ጽጌ የተባለች እናቱ ድንግል ማርያም ፍሬ የተባለ ልጇ እሱን ኢየሱስ ክርስቶስን አዝላ ከኢየሩሳሌም ምድረ እስራኤል ወደ ግብጽ እንዲሁም ወደ አገራችን ኢትዮጵያ የተሰደደችበትን በማሰብ ለአርባ ቀናት ያህል ምዕመናን በፈቃዳቸው ለበረከት ይፆማሉ:: ሊቃውንቱም ከምሽቱ ሶስት ሰዓት እስከ ንጋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ድረስ «ጽጌ ጽጌ ዘሰሎሞን ወዳዊት ጽጌ አሮን ዘክህነት» እያሉ ያመሰግኗታል:: እመቤታችንም በስደቷ ወራት ብዙ መከራ ደርሶባታል ተርባለች ተጠምታለች ልጄን ይገሉብኛል ብላ ተጨንቃለች::
ጌታ ወደ ግብጽ የተሰደደው ለምንድን ነው ቢሉ?....
(አንደኛ)..ነቢዩ ኢሳያስ የተናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው:: «ወይወርድ እግዚእነ ተጽእኖ ድበ ደመና ቀሊል» «ጌታችን በፈጣን ደመና ሆኖ ወደ ግብጽ ይወርዳል» ኢሳያስ 19 ቁ. 1
(ሁለተኛ).. በግብጽ አምልኮተ ጣኦት ብዝቶ ነበር እና አምልኮተ ጣኦትን ለማጥፋት ነው::
እመቤታችን ሶስት አመት ከስድስት ወር እስኪፈጸም ድረስ በብግጽ እናም በሀገራችን በኢትዮጵያ የስደት ጊዜ አሳልፋለች ማቴ..2 ቁ. 19
በስደት ከቆዩ በኋላ ሄሮድስ ሞተ።.....ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ «የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ አለው፡፡ እርሱም ተነስቶ ሕጻኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ሀገር ገባ» ማቴ 2-19-21/
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 ቀን ጀምሮ እስከ ኅዳር 6
ቀን ድረስ የጌታን እና የእመቤታችንን ስደት በማሰብ የጽጌ ፆም ይፆማል
እንኳን አደረሳችሁ!!!