Showing posts with label ዜና. Show all posts
Showing posts with label ዜና. Show all posts

20121103

ዘማሪት አቦነሽ አድናው ከኪነጥበብ ጋደኞቿ የሽኝት ፕሮግራም ተደረገላት

በትላንትናው ዕለት በተደረገው የእራት ግብዣ ለዘማሪት አቦነሽ አድነው መሸኛ ብዛት ያላቸው አርቲስት ጓደኞቿ በተሰበሰቡበት ንግግር በማድረግ የዘፋኝነት ስራዋን ለቃ ወደ እግዚአብሔር  አመስጋኝነት ወደ ዘማሪነት የተሸጋገረችና ለመጨረሻ ጊዜ የዘፈኑን ዓለም የተወችና ያቆመች መሆኑን ለአርቲስት ጓደኞቿና በዕለቱ ለነበሩት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ተናግራለች። አቦነሽ ስትናገር እኔ ለ24 ዓመት በሙዚቃው አለም አገልግያለሁ ሙዚቃን በጣም እወድ ነበር ሙዚቃ ለኔ ትልቅ ባለውለታዬ ነው አለምን አዙሮ አሣይቶኛል እኔም አድጌበታለሁ ሙዚቃ ለህይወቴ ብዙ አስተዋፅኦ አድርጎልኛል። ኑሬበታለሁ ቤተሰቦቼን ረድቼ ልጆቼን አሣድጌበታለሁ። ግን ዘማሪ መሆንን የተመኘሁትን ያህል ድምፃዊ መሆንን ተመኝቼው አላውቅም ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ልቤ ሸፍቷል ሁል ጊዜ አስበው ነበር ዘማሪ መሆን እግዚአብሔርን ማገልገል የበለጠ ዋጋ ያለው መሆኑን አውቅ ነበር። እናም እግዚአብሔር ይመስገን ተሳካልኝ ሀሣቤ ሞላልኝ ይሄው ዛሬ በምወዳችሁ የጥበብ ጓደኖቼ መካከል ከአሁን በኋላ ዘማሪ ነኝ! ለወደፊትም መፅሀፍ ቅዱስ ቁጥር እየጠቀስኩ ብዙ ስለ እግዚአብሔር ልነግራችሁ እወዳለሁ ስትል ጓደኞቿን ተማጥና ከዘፈን ዓለም መሠናበቷን አብስራለች። በእለቱ የተሰበሰቡት ጓደኞቿም ለአቦነሽ(አቢቲ) ያላቸውን ክብር ገልፀው። በጭብጨባ የስራ መልቀቂያ ፈቃድ ሰጥተው በዘፈን አለም በነበረችበት ጊዜ አብረዋት ስላሣለፉት ስለ ፅባይዋ በጣም ንፁህ ደግ ቅንና ከበፊትም በዘፈን ዓለም ላይ እያለችም ከአፏ የሚወጡት ከአንደበቷ የሚፈልቁት ቃሎቿ የተቀደሱ ክፉ ነገር የማይወጣት የዘፈነችው የሚያምርባት ስትስቅ ስትጫወት ተወዳጅ የሆነች ትሁት በመሆኗ የመረጠችው መንገድ የሚገባትና ጥሩ የእግዚአብሔር አገልጋይ ልትሆን የምትችል መሆኗን በዕለቱ እየተነሡ ምስክርነት ሰጥተዋል። በምሽቱ የእራት ግብዣ ላይ አብረዋት ሲዘምሩ ሲያሸበሽቡ ብሎም በግጥም ስንኝ የቋጠሩላትም አንጋፋ አርቲስቶችም ነበሩ።
ተነሡ ለምስጋና(3)
ለዚህ ላበቃን እንዘምርለት
በዙፉኑ ፊት እንስገድለት!
እያለች አዲስ የሰራችውን መዝሙር በጣፋጭ ድምጿ ስትዘምር ከፊቷ ደስታና ብሩህ ህይወት ይታይባት ነበር።
በዕለቱ ከነበሩት ታላላቅ አርቲስቶች መካከል ታላቋ የኪነ-ጥበብ ሰው አርቲስት አለምፀሃይ ወዳጆ ስለ አቢቲ የሙዚቃ አነሣስና ታሪክ በጥቂቱ እንዲህ ስትል ተደምጣለች።
አቢቲ የተወለደችው በደቡብ ኢትዮጵያ በሃይቆችና ቡታጅራ አዉራጃ በሶዶ ወረዳ ቡኢ በምትባል ትንሽ ገጠር መንደር ሲሆን በጊዜው የነበሩት የሙዚቃ ጥበብ ባለሙያዎች ወደ አቢቲ መንደር ወደ ቡኢ በወረዱበት ጊዜ አቢቲን ለሙዚቃ አጯት። እሷም ሁል ጊዜ በዚህ በኪነጥበብ ሙያ ውስጥ ባለውለታዋ የሆኑትን ኮረኔል ለማ ደምሠውንና አርቲስት አየለ ማሞን ሁልጊዜ ታነሣለች። አቢቲ ገና ሙዚቃን የጀመረችው በድሮው የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡደን ውስጥ ነው ሀ ብላ ሙዚቃን የተቀላቀለችው። ከዚያ በኋላም ባሳተመችው “ባላገሩ” “ባህሌን” በተሰኙ ሲዲዎቿ  ተወዳጀነትን ያተረፈች ሲሆን አቢቲ መቼም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ህይወት ሁላችን አርቲስቶችም ሆንን የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያውቀው ሙዚቃን ደምቃበታለች፣ አለምን ዞራበታለች፣ ታጅባበታለች፣ ተምነሽንሻበታለች በትላልቅ መድረኮች ላይ የመስራት እድል አግኝታበታለች። በዚያም መጠን ደግሞ ተወቅሣበታለች፣ ተከሣበታለች፣ በሬዲዮ ተወግዛበታለች እናም በተለያዩ ሁኔታዎች በማለፍ የሙያ አስተዋፀኦ አበርክታበታለች። አቢቲ ገና ስትጀምር ጀምሮ ከታላላቅ አርቲስቶች ከነ ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ከነ ብዙነሽ በቀለ እና ሌሎችም በነበሩበት የጀመረች በመሆኑ እስከ መጨረሻው በዚህ በአሜሪካም ከታላላቅ አርቲስቶችና ታላላቅ መድረኮችን የማግኘት እድልም አግኝታለች። በግሏ በአቢቲነቷ  በአለም አቀፍ መድረክ እንደነ ኬኔዲ ሴንተር ባሉ ቦታዎች በመገኘት ተጫውታ ሌሎችንም ተከታዮችና አድናቂዎችን ያገኘች አርቲስት ናት።
እግዚአብሔር ለዚህ ካበቃሽ እንግዲህ እኛም ያንቼን እድል ይስጠን እያልን ባለችበት ፀንታ፣እንድትቆይ እየፀለይን እየደገፍናት፤ እያገዝናት የሀሣቧ ተከፋይ እየሆንን እንዳንለያት። እኛንም እንደ እሷ እንዲያበቃን እንፀልያለን። አቢቲ ታመሽ በነበርሽበት ወቅት ድጋሜ ህይወት ከሠጠኽኝ ጌታዬ ለአንት አገልጋይህ እሆናለሁ ባልሽው መሠረት ባገኘሽው ድጋሜ ህይወት አምላክሽን ለማመስገን መልካሙን መንገድ መርጠሻልና ስምሽም ገና ከማለዳው የተሠጠው “የአቦ ነሽ” ነውና አቦዬ ብርታቱን ፅናቱን እንዲሰጡሽ በእኔና በጓደኞችሽ ስም እመኝልሻለሁ በማለት አርቲስት ዓለምፀሃይ ወዳጆ እና ሌሎችም ጓደኞቿ መልካሙን በመመኘት ስትዘምር እየዘመሩ፣ ስታሸበሽብ እያሸበሸቡ፣ ምሽቱን አብረዋት በመሆን ድጋፋቸውን በመስጠት ከእንግዲህ ወዲህ እንደድሮው አብረዋት በአለማዊው መድረክ የማይቆሙ መሆኑን ሲያውቁ የትካዜ መልክ ቢታይባቸውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተክርስቲያን አማኞች በመሆናችን ወደ አንቺ የምንመጣበት አንችን ፈልገን የምንመጣበት መልካም ቦታ ላይ ስለምናገኝሽ እንዳልራቅሽን በመገመት በደስታ ጥያቄሽን መልሠናል መልካሙን ሁሉ ይግጠምሽ ብለዋታል። በእለቱ በነበሩት ወጣት ዘማሪያን መካከል ዘማሪ ቸርነተ ሰናይ ዘማሪ ያሬድ እና የመዝሙር ዜማና የግጥም ደራሲዉ ሊቀ ትጉሃን መኩሪያ ጉግሳና ሰባኪ ቀሲስ ተስፋዬ መቆያ እንዲሁም ዲያቆን ቢኒያም እና ሌሎችም የተገኙ ሲሆን በምሽቱ የተገኙትን አርቲስቶች አመስግነዉ የዛሬዉ ዝግጅት በእናንተ የተዘጋጀ መሸኛ ነዉ።
እኛ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ደግሞ ለእህታችን ለዘማሪት አቦንሽ አድነዉ ኖቬምበር 21.2012 በ 845 ኖርዝ ሃዋርድ ስትሪት አሌክሳንድሪያ ቨርጅኒያ በመናደርገዉ ዝግጅት ላይ በምናዘጋጀዉ የአቀባበል ዝግጅት ላይ እንድትገኙልን እናሳስባለን። በእለቱ ታዋቂ ዘማሪያን ዘርፌ ከበደ፣ ቸርነት ሰናይና ሌሎችም እዉቅ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዘማሪያንና ታዋቂ ሰባኪያን እንዲሁም ህዝበ ክርስቲያኖች የሚገኙ መሆኑን ገልጸዉ ምሽቱን በምርቃት አክትምዋል።
ምንጭ ባዉዛ ጋዜጣ



20121019

የኢትዮጵያ ፓርላማ አባላትን "እግዚአብሔር ኢትዮጵያን በበረከቱ ይጎብኛት " መባሉ አሳቃቸው

የማክሰኞዉን  የፓርላማ ዉሎ አላየሁትም ነበር። ብቸኛው  የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ንግግራቸውን ሲጨርሱ "እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሀገራችንን በበረከት ይጎብኛት" በማለታቸው አፈ ጉባኤዉን አባ ዱላን ጨምሮ የፓርላማ አባላቱ እንደሳቁ የሚያሳየዉን ቪድዮ ሳይ  እጅጉን ነበር ያዘንኩት ግራም ተጋባው። የ እግዚአብሔር ስም መጠራቱ  እንዲህ የሚያስቅ ከሆነ  እነርሱ የሚያመልኩት ምን ይሆን? የ እኛ ሀገር መሪዎች ስልጣኔ ነት መስሏቸው ነው እንዳልል ያደጉ አገራት መሪዎች ከንግግር በኃላ እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ ብለው ሲናገሩ አንድም ቀን ሰው ሲስቅ አይቼ አላቅም። ታዲያ ምን የሚሉት ይሆን የ እኛ ሀገር መሪዎች እንዲህ ድዳቸው እስኪታይ መሳቃቸው ከምን የመነጨ ነው? እኔ ግን በማመን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንን እና ህዝቦቻን ይባርክ እላለው አሜን እስቲ እናንተም ይሄንን ሺድዮ  ተመልከቱ

20120913

ድምጻዊት አቦነሽ አድነው ዘፈን አቁማ ዘማሪት መሆኗን አስታወቀች


"ባላገሩ" በተሰኘው አልበሟ የምትታወቀው ድምጻዊት አቦነሽ አድነው ሙዚቃ ማቆሟን እና ወደ ዘማሪነት መግባቷን ይፋ አደረገች::
ድምጻዊቷ ካሁን በኋላ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስርዓት መሰረት እግዚአብሔርን አመሰግነዋለዉም ብላለች::
"ይህን ዉሳኔ ለመወሰን 5 ኣመታት ያህል ፈጅቶብኛል " ያለችው ድምጻዊቷ "ማታ ማታ ስዘፍን  ቃሉን እራብ ነበር ጠዋት ቤተክርስትያን ለቅዳሴ ባልደርስም ቃሉን ስመቼ ስመለስ ልቤን ያጸናልኝ ነበር " ካለች በኋላ "በአዲሱ አመት አሮጌዉ ማንነቴን ቀይሮ እዚህ በ ቤቱ እድገኝ እና ቆሜ እንድዘመር  እግዚአብሔር ስለረዳኝ አመሰግለዋለው "በማለት
 "አበረታኝ ክንድህ ጌታዬ
አበረታኝ ፍቅርህ አምላኬ
 በስምህ ድኛለው ፀጋህ
በማደሪያህ ሆኘ ስጠራህ "የሚለዉን የዘማሪ ዳግምዊን  መዝሙር ዘምራለች:: ቀሲስ መምህር ተስፋዬ መቆያ አያይዘው እንደተናገሩት የጠፉ ወገኖቻችን ተመልሰው ለጌታ ክበር እንዲዘመሩ ሁላችንም በፍቅር በአንድነት እንቁም የሚል መልክት አስተላልፈዋል::
የቀድሞዋን ድምጻዊት አቦነሽ አድነዉን ምስክርነት የሚያሳየዉን video ይመልከቱ


20120904

በጀርመን የሚገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ማህበር ካህናት አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ጠየቁ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
በጀርመን ሀገር በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ሆነን  በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የአደራ ቃል መሠረት በንጹሐን አባግዕ የተመሰሉ ምዕመናንን ተግተን በመጠበቅ ቤተ ክርስቲያንንም በማገልገል ላይ የምንገኝ የማኅበረ ካህናት የጋራ ያቋም መግለጫ።

በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስቅዱስ እናተን   ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ   የሐሥ ፡20፡28-30



መሪዋና አጽናኞዋ መንፈስቅዱስ የሆነችው ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለያዩ  ዘመናት ብዙ የፈተና ጊዜያትን ተቋቁማ በማለፍ ተወዳዳሪ የማይገኝላት ቤተ ክርስቲያን መሆኗ ለማንም የተሠወረ አይደለም ።
   ለምሳሌም ያህል፦ የዮዲትንና የግራኝን  የመከራ ዘመን ብቻ መጥቀሱ ከበቂ በላይ ነው ማለት ይቻላል ።ወደዝዝር ሁኔታው  ለመግባት አሁን አስፈላጊ ስላልሆነ እናልፈዋለን ። አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት የሰበሰቧት ቤተክርስቲያን  ባሳለፈችው የመከራ ዘመን ሁሉ አንዲት በመሆኗ ችግሩን በአንድነት መንፈስ ተቋቁማ  እስከ አሁን ድረስ ያለምንም ችግር ደርሳለች ።ይችን ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያን ለማዳከም በየጊዜው  ከውስጥም ከውጭም ያልተጠነሰሰ ሴራ የለም በውጭ በኩል ስናይ የምዕራባውያኑ የዕምነት ድርጅቶች ወቅትና ጊዜን በመጠበቅ ልጆቿን ምእመናንን ከጉያዋ እየነጠቁ የነሱን ዕምነት እንደ ህጻናት ወተት ግቶ በማሳደግ በዚች ቤተ ክርስቲያን ላይ በጠላትነት እንዲነሱ ማሰለፍ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሀገሪቱ መንግሥት በየጊዜው  በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ቤተ ክርስቲያኗን እየጎዳት ይገኛል። የሩቁን ትተን የቅርቡን  ብቻ እንኳ ብናይ በደርግ ዘመነ መንግሥት በቅትታ የቤተ ክርስቲያኒቱን  እንቅስቃሴ የሚከታተል ከመንግስት ሥራ አስኪያጅ እየተመደበ የቆየ ቢሆንም ከደርግ ውድቀት በኋላ ሀገሪቱን በኃይል የተቆጣጠረው የኢህዴግ መንግሥት ደግሞ ከቀድሞ በከፋ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጫናውን ከባድ እንደ አደረገው በለፉት  ዓመታት በግልጽ ታይቷል አሁንም እየታየ ያለ ችግር ነው።ምክንያቱም ቤተክህነቱ የቤተ ክርስቲያኗ ሳይሆን የመንግሥት ተቋም እስኪመስል ድረስ በሰፊው እጁን አስገብቶ በመሥራት ቤተ ክርስቲያኗን ሲያምሳት ቆይቷል ።በዚህም ምክንያት ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይህን ድርጊት  እየተቃወሙ ህይወታቸው አልፏል።
በደርግ ዘመን የነበረው ማእበል በኢህዴግ ዘመን ሞገዱ በርትቶ ከፍ ብሎ ከቤተ ክርስቲያኗ  ጉልላት ላይ በመውጣት እሱ የፈለገውን ፓትርያርክ በማስቀመጥ ቤተ ክርስቲያኗን ደፈረ፤ አባቶችን በመከፋፈል ጣልቃ በመግባት ዓላማው እንዲሳካለት አደረገ፤  ይህም ሊሆን የቻለው ብጹአን አባቶች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለዚች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ህልውና ቅድሚያ በመስጠት  በአንድነት  ሊቆሙ ባለመቻላቸው ነው።




በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይኖት ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ  በቅዱስ ሲኖዶስ ምላዓተ ጉባኤ የተመረጡት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በመልካም ጤንነትና በህይወት እያሉ የመላ ሕዝበ ክርስቲያኑና ካህናቱ ድጋፍ ሳይለያቸው መንበራቸውን በኃይል እንዲለቁ  መደረጉ ሁሉም የሚያውቀው እውነት ነው። እንደተለመደው በፈቃዳቸው ነው የለቀቁት ተብሎ እንዳይዋሽ በወቅቱ ፓትርያርኩን ከስልጣናቸው አስገድደው ያወረዱት ጠቅላይ ሚንሥተር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ፓትርያርኩን ከመንበራቸው አውርደው ለቤተ ክርስቲያኗ መለያየት ምክንያት መሆናቼው እንደሚጸጽታቸው በዓለም መድረክ ላይ ቀርበው የተሠራውን  ስህተት አምነዋል ።
አቶ ታምራት ላይኔን መንፈስቅዱስ አፋቼውን ከፍቶ ፊታቸውን ጸፍቶ ያናገራቸው ጠቢቡ ሰሎሞን  ለሁሉም ጊዜ አለው ባለው መሠረት እውነትና ንጋት እያደር እንደሚባለው የአባቶቻችን አምላክ ይሄን በማድረጉ ሎቱ ስብሐት ብለን  እናመሰግነው አለን።  ምንም እንኳን ያለፈውን ነገር ለታሪክ ባለሟያዎች ብንተወውም ለማስታወስ ያህል መጥቀሱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም አንድ ነገር መዘንጋት የለበትም ። ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ መንበሬን አለቅም ብለው በነበረበት ጊዜ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በአንድነት ከጎናቸው ቁመው ቢሆን ኑሮ  ዛሬ ላለንባት ለቤተ ክርስቲያኗ መከፋፈል ባልተደረሰም ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመራው አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በደነገጉለት ቀኖና ነው። ቀኖና ቤተ ክርስቲያኑ የሚያዘው አንድ ፓትርያርክ በኅይወት እያለ መንበሩን መልቀቅ እንደሌለበት የሚደነግገው አንቀጽ ተጥሶ በሕጋዊው ፓትርያርክ ላይ ህገ ወጡ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ 5ኛ ፓትርያርክ በመባል በመንበሩ ላይ እንዲቀመጡ ተደረገ የወያኔ መንግሥት የፈለገውን ዓላማ ለማሳካት ብሎ  ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጥሶ  ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አፍርሶ  አቡነ ጳውሎስን በቅዱሱ መንበር ላይ ቢያስቀምጣቸውም በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጭ የሚገኝ ሕዝበ ክርስቲን አንድ ቀን አባትነታቸውን ሳያምንባቸው ሃያ ዐመት ሙሉ በተቃውሞና በውግዘት  ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ከሀገር  ውጭ በስደት ሁኖ የቤተክርስቲያንን ሥራ በመሥራት  ላይ ካለው በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋርም ተወጋግዘዋል ውግዘቱም  ሳይፈታ የሰላምና የአንድነት ጉባኤ በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የሽምግልና ሥራ እየሠራ በአለበት በዚህ ጊዜ ፤ምዕመናንና ምዕመናት ሁለቱም ሲኖዶሶች የቤተ ክርስቲያኗን አንድነት ከነገ ዛሬ ያስተካክላሉ ብለው በተስፋ ሲጠብቁ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየተዋል ።ይህም ማኅበረ ካኅናቱን እጅግ ያሳዘነ ዐቢይ ጉዳይ  መሆኑን ሳንገልጽ አናልፍም።ምክንያቱም በሕይወት እያሉ የተበላሸው ተስተካክሎ የተጣሰው ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ተመልሶ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ችግር በእርቀ ሰላም ተፈትቶ ቢሆን ኖሮ  ለሁሉም  ቀላል ይሆን ነበር ።
 ነገርግን ይህ ባለመሆኑ የገባያ ግርግር ለቀጣፊ ይመቸዋል እንደሚባለው ለቤተ ክርስቲያኗ አንድነት ከማሰብ እና ጸሎት ከማድረግ ይልቅ የዚች ቤተ ክርስቲያን ተለያይቶ መቅረት የሚያስደስታቸው በመለያየቷ ምክንያት የላይ ፈሪ የታች ፈሪ በማለት ከሁለቱም ክፍል ፍርፋሪ የሚለቅሙ የውስጥ ጠላቶች በየድህረገጹ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ ሲያናፍሱ በመታየታቸው የቤተክርስቲያን መሥራች የሆነው አምላክ አበው ልብ ይስጣቸው እንላለን።
እስካሁን ቤተ ክርስቲያኗን ለሁለት የከፈለው ጉዳይ በራሱ በእግዚአብሔር ፈቃድ አንደኛው አባት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ስለዚህ አሁን በህይወት ያሉት ቀድሞም ያላግባብ በመንግሥት ኃይል ከሥልጣናቼው እንዲወገዱ የተደረጉት  አባት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደመንበራቼው ሊመለሱ ይገባል። ይህም ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያ የሚገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለቤተ ክርስቲያኗ አንድ መሆን በአድነትና በቅንነት ሲቆሙ ብቻ ነው።
ይህ ካልሆነ ግን ባለፉት ሃያ ዓመታት እንኳ የተለያዩ  ጥናቶች እንዳመለከቱት በቤተ ክርስቲያኗ መከፋፈል ምክንያት ወደ14 ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናን ወደሌላ ቤተ ዕምነት እንደሄዱ ተረጋግጧል።
 ቅዱስ ሲኖዶስ ካለፈው ስህተት ተምሮ ለቤተ ክርስቲያንና ለምዕመናን አንድነት ሲል ቀኖናዉን መልሶ መጠበቅና ማስጠበቅ ይገባዋል እንላለን። ያለፈው ስህተት እናዳይደገም  በታሪካዊቷና ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ የታሪክ ጠባሳ ለትውልዱ እንዳይተላለፍ ፤ትውልዱም በአባቶች ላይ እምነት እንዳያጣ በኢትዮጵያ ያሉ የቅዱስ ሲኖዶስን አባላት በቤተ ክርስቲያን አምላክ እያሳሰብን የሚከተለውን  ያቋም መግለጫ እናስተላልፋለን። 


  1. አሁን በስደት ላይ ያሉት አባት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በስቸኳይ ወደመንበራቸው እንዲመለሱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በፍጹም ፍቅርና አንድነት የተጣለባችሁን መንፈሳዊ ግዴታ በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ እንድታስወግዱ ፤ቤተ ክርስቲያንን እንድትጠብቋት መንፈስ ቅዱስ እናተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው እና ለራሳችሁ ልትጠነቀቁ ይገባል የሚለውን ቃል እንድትፈጽሙና ከታሪክ ተጠያቂነት እንድትድኑ። ይህ ባይሆን ግን በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ከቀድሞ በከፋ ሁኔታ የልዩነት አድማሱ የእየሰፋ እልባት ወደማይገኝለት ችግር እየገባን እንደሆነ ከወዲሁ እንድታውቁ እና እንድታስቡበት እንጠይቃለን፤
  2. በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተጋረጠው ችግር ሳይፈታ ለሹመት የሚሯሯጡትን የቤተ ክርስቲያንና የሀገር ጠላቶች በጽኑ እንቃወማለን፤
  3. የኢትዮጵያ  ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፤ አባቶች ካኅናት፤ዲያቆናት፤የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች መላው ህዝበ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን ቀኖና እደቀድሞው እንዲስተካከል ወደፊትም ተጠብቆ  እንዲኖር በጸሎትም በሀሳብም እድትረባረቡ በቤተ ክርስቲያኗ ስም እንሳስባለን፤
  4. መንግሥት እስካሁን በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የሠራውን ስህተት አርሞ እጁን ከቤተ ክርስቲያኗ ላይ በማንሳት ለቤተ ክርስቲያኗ አንድነት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍና በስደት ያሉት ፓትርያርክ ወደመንበራቸው ተመልሰው መለያየት ተወግዶ ሁሉም ለአንዲት ኢትዮጵ በጋራ እንዲረባረብ እንቃፋት ከመሆን  እንዲታቀብ እንላላን፤
  5. በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካና የኅሊና እሥረኞች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ ከሥር ተፈትተው እንደማንኛውም ኢትዮጵዊ ዜጋ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን በነጻነት  እንዲገልጹ እንጠይቃለን፤
  6. በአሁኑ ሰዓት አገሪቱን እየመራ ያለው መንግሥት ከመቼውም በላይ ለሰላም በመነሳት  እና ከተቀዋሚዎች ጋር በመስማማት ብሔራዊ እርቅ ሁኖ በሁሉም የተቃውሞ ጎራ ያሉት ወገኖች የሚሠሩት  ለሀገርና ለህዝብ እስከሆነ ድረስ እርቀ ሰላም እንዲመሠረቱና ሀገራችንን የሰላም ቀጠና በማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተቻችሎና ተከባብሮ በመኖር አብሮ የመኖር እረዕያችን እውን እንዲሆን ፈቃደኝነትን እንዲያሳዩ ስንል እናሳስባለን።
በመጨረሻም ሁሉን በፈቃዱ ማድረግ የሚቻለው ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያሉትን  የአባቶቻችን አንድነት እንዲያሳየን እንለምነው አለን ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፤
ነሐሴ 26 ቀን 2004 ዓ.ም
ጀርመን ፍራንክፈርት

20120820

የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ምርጫ አስመልክቶ ከቅዱስ ሲኖደስ ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ



ሕገ ቤተ ክርስቲያን ስለ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ

አንቀጽ 17
·              ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
1.    ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤመንበረ ፓትርያርክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫም ይካሔዳል፡፡
2.    የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደሥራው ሁኔታ እየታየ 40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይሆናል፡፡
3.    የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ተግባር
ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ጊዜያዊ ጉደዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር እየመከረ ያከናውናል፡፡
በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ሆኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም::

ምንጭ፦ ሕገ ቤተ ክርስቲያን 1991 .
.

ሰበር ዜና ቅዱስ ሲኖዶስ አቃቤ መንበር ሰየመ


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ አቃቤ መንበር ሰየመ፡፡ በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቃቤ መንበር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ፓትርያርክ እስኪመርጥ ድረስ ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት ይመራሉ፡፡
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 

20120509

ለንግሥ ወደ ርእሰ አድባራት ተድባበ ማርያም ገዳም የተጓዙ 17 ሰዎች በመኪና አደጋ ሕይወታቸው አለፈ

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን አማራ ሳይንት ወረዳ በምትገኘውና ዛሬ በምትነግሠው ርእሰ አድባራት ተድባበ ማርያም ገዳም ለንግሥ በመጓዝ ላይ የነበሩ 17 ሰዎች፣ በደረሰባቸው የመኪና መገልበጥ አደጋ ከትናንትና በስቲያ ሕይወታቸው ማለፉን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ከትናንት በስቲያ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን በደረሰው የመኪና መገልበጥ አደጋ 17 ሰዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው ማለፉን፣ ሁለት ሰዎች ወደ ደሴ ሆስፒታል መላካቸውን፣ ሁለት ደግሞ ሳይንት አጅባር ህዳር 11 ሆስፒታል መግባታቸውንና አንድ ተጐጂ ደግሞ ሳይንት አጅባር ጤና ጣቢያ ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ እማኞቹ ተናግረዋል፡፡

ሕይወታቸው ካለፉት 17 ሰዎች መካከል አሥሩ እዚያው ተድባበ ማርያም ገዳም የቀብር ሥርዓታቸው በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 11 ሰዓት መፈጸሙን፣ የቀሪዎቹ አስከሬን ወደ አዲስ አበባና ወደየመጡበት አካባቢ እየተሸኘ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በ600 ኪሎ ሜትርና ከሳይንት አጅባር በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የተድባበ ማርያም ገዳም ለመድረስ ጥቂት ርቀት ሲቀር ባለው ገደላማ ቦታ ላይ ሲደርስ፣ አንድ መነኩሴና ሁለት ወጣቶች ወርደው በእግራቸው መጓዝ በመጀመራቸው ከአደጋው መትረፋቸውን እማኞቹ ገልጸዋል፡፡ በመኪና አደጋው ሕይወታቸው ላለፈውና የቀብር ሥርዓታቸው በዚያው በገዳሙ ለተፈጸመው ምዕመናን ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በተገኙበት በፈረንሳይ አቦ ቤተ ክርስቲያን ትናንት ምሽት ላይ ፀሎተ ፍትሐት መደረጉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

 ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እንመኛለን !!!!

                                                                                              ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ 

20111221

ታላቅ ዜና ቤተክርስቲያን

“ቤተ መቅደስህ ቅዱስ ነው በጽድቅም ድንቅ ነው።” መዝ. 65፡ 5

ቀዳማዊ ዜና
የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን

በንብ የሚጠበቀው የቦሌ በሻሌ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወአቡነ ሠላማ ቤተክርስቲያን በሕዳር 12 / 2002 ዓ.ም ለሚከበረው የቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በዋዜማው ሕዳር 11 ቀን ዋዜማ ቆመው ሳለ ከምስራቅ አቅጣጫ አውራውን አስቀድሞ እየተመመ የመጣው የንብ መንጋ ቤተክርስቲያኗን ዞሮ ጣራዋ ሸራ ግድግዳዋ ሳጠራ ወደሆነችው ቤተመቅደሷ ብቻ በተሰራው (ቅድስት እና ቅኔ ማኅሌት የሌለው አነስተኛ መጠን ያላታ ቤተክርስቲያን ላይ) የቃልኪዳኑ ታቦተ ሕግ ባረፈበት መንበር ውስጥ መንጋው ንብ ገብቶ ሰፍሯል። የንቡ መንጋ ወደ መንበሩ ሲገባ በአገልግሎት ላይ ያሉትን ካህናት ሳይነካ አገልግሎቱም ሳይታጎል አድሯል። በሕዳር 12 ምንም እንኳን ካህናቱ ስጋት ቢገባቸውም ታቦተ ሕጉን ማውጣት ግዴታ ነውና አስፈላጊውን ስርዓተ አምልኮ ከተፈፀመ በኋላ ታቦተ ሕጉ ከመንበረ ክብሩ ሲወጣ የንቡም ሠራዊት ከመንበሩ በምስራቅ በኩል ወተው አንድም ምዕመን ሳይነድፉ አብረው ከታቦቱ ጋር አክብረው ወደ መንበሩ ሰፍረዋል። አሁንም በመንበሩ ውስጥ ይገኛሉ። የመንበር ውስጥ ማርም ማኅበረ ምዕመናኑ እየበላ ከቅዳሴ ፀበሉ ጋር እየጠጣ ድኅነተ ሥጋና ድኅነተ ነፍስን እያገኙ ይገኛሉ።
ሊቃውንት ይህን ተዓምር ሲተረጉሙ፡ ንቡ ሠራዊተ መላእክት (ነገደ ቅዱስ ሚካኤል) ናቸው ብለው በዕለቱ አስተምረውናል ይህም በተግባራቸው የተገለጸ ነውና እንደምን ቢሉ ከቀናት ተመርጦ በሕዳር 12 ዋዜማ መምጣታቸው ሕዳር 12 ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ተብሎ የተሾመበት እስራኤላውያንን ከግዞት አውጥቶ በምድረበዳ የመራበት መናን ያዘነበበት መታሰቢያ ዕለት ነውና በበዓለ ሲመቱ ክቡራን ንዑዳን የሚሆኑ ሠራዊተ መላዕክት በምስራቅ በኩል በምትገኘው በስተምስራቅ በኩል ስብሐተ እግዚአብሔር በሚደርስበት ሰዓት መተዋልና ነው። አንድም በአካባቢው የተለያዩ ዛፎች እንዲሁም መኖሪያ ቤቶች ሳሉ በዚህች ቅድስት ቤተመቅደስ ውስጥ የቅዱስ ሚካኤል እና የቅዱስ እስጢፋኖስ ታቦተ ሕግ ባለበት መግባታቸው ሠራዊተ መላእክት ናቸው በማለት ተዓምሩን ተርጉመዋል።
አዲስ ዜና
በሕዳር (ልብ ይበሉ ሁለቱም ታላላቅ ዜናዎች የተፈጸሙባቸው ወር አንድ ናቸው “ወርሐ ሕዳር”) በሕዳር 21 ቀን 2004 ዓ.ም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ የሆነችው ታቦተ ጽዮን ዳጎንን ድል አድርጋ በክብር የተመለሰችበትን በዓል በሚከበርበት ዕለት ካህናት በሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ሳሉ ከየት መጣ ተብሎ የማይታወቅ እጅግ ብዙ የሆነ የንብ መንጋ ዳግም ወደዚህች ቤተክርስቲያን መጣ። ድምፁ ያስደነገጣቸው ቀዳስያን ካህናት እና ምዕመናን (በቁጥር እጅግ ጥቂት የሆኑ) ምን መጣ? ወይስ የመንበሩ ንቦች ወጡን? በማለት ሲደናገጡ ከዲያቆናት መካከል አንዱ ወጥቶ ቢመለከት በጉልላቱ ስር የመስቀል ምልክት ሰርተው በጣራው ላይ ብዙሃኑ ሲያርፉ የቀረው ቤተክርስቲያኗን ይዞራል። “በልዎ ለእግዚአብሔር ግሩም ግብርከ፡ እግዚአብሔርን ስራህ ድንቅ ነው በሉት” እንዳለ እጹብ ከማለት በቀር ምን ማለት ይቻላል? ይህም የንብ ሠራዊት ሥርዓተ ቅዳሴው ሲያበቃ አዲስ በተሰራችው፣ በመጠኗ አነስተኛ የሆነውችው ቤተልሔም ውስጥ ገብቶ ሰፍሮ ይገኛል። ከደብሩ አገልጋይ ካህናት ውስጥ አንዱ ቄስ ገብተው ሲያጥኑና የንቡን ሁኔታ ሲመለከቱ ከመግባቱ ገና በ10ኛ ቀኑ ማር ለመስራት የሚያስፈልገውን የመጀመሪያ ደረጃ እንደጀመረ የደብሩ አስተዳዳሪ መልዓከ ፀሐይ ሲራክ ገበየሁ በታሕሳስ 1 ቀን 2004 ዓ.ም በተዘጋጀው ልዩ መርሐ ግብር ላይ ለምዕመናን ተናግረዋል።
በደብሩ እየተደረጉ ካሉ ተዓምራት ውስጥ ለአብነት ያህል፡
v በከባድ የራስ ምታት በሽታ (ማይግሬን) ለ15 ዓመታት ሲሰቃዩ የነበሩ አንድ ምዕመን ከመንበሩ ውስጥ በወጣችው አንድ ንብ ራሳቸውን ተነድፈው ድነዋል።
v በእብድ ውሻ ተነድፎ ይሰቃይ የነበረ ምዕመን በህክምና ማዕከል የውሻውን አንገት ካላመጣህ ልትድን አትችልም ተብሎ እየተሰቃየ የነበረ በቦታው መጥቶ በሁለት ንቦች የተነከሰበት ቦታ ተነድፎ ከበሽታው ሙሉ በሙሉ ድኗል።
v አንዲት ምዕመን ለ5 ዓመታት ያህል በአእምሮ በሽታ አብዳ ቤተሰቦቿን የማታውቅ የነበረች ከማሩ ጸበል ወስደው ቢያጠጧት በ5ኛው ቀን ድና ምስክርነት ሰጥታለች።
v በኪንታሮት በሽታ ለብዙ ዘመናት ሲሰቃይ የነበሩ ምዕመን ከመንበሩ የተቆረጠውን ማር ተቀብተው ድነዋል።
v ለብዙ ጊዜ መስማት ተስኖት የነበረ ምዕመን ማሩን በጥብጦ በጆሮው ውስጥ ቢከት ወዲያው ድኖ መስማት ችሏል።
v እጅና እግሯ ሲንቀጠቀጥ የነበረች ሴት በፀሎት ላይ ሳለች በአንድ ንብ ተነድፋ ወዲያውኑ ከበሽታዋ ድናለች።
v በአስም፣ በጨጓራ፣ በኩላሊት፣ በደም ግፊት፣ በጭንቀት በሽታ ሲሰቃዩ የነበሩ ምዕመናንም ማሩን ጠጥተው፤ ከመንበሩ በሚወጡ ንቦች ተነድፈው ድነው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

“ምንተ ንግበር አሀዊነ፡ ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ።” (ሐዋ. 2፡ 37)
ይህች ቅድሰት ቤተክርስቲያን እጅግ ብዙ የሆነ ገቢረ ተዓምራትን እያደረገች የምትገኝ የሠማይ ደጅ ናትና ገና ብዙ ምዕመናን ድኅነተ ሥጋንና ድኅነተ ነፍስን የሚያገኝባት ናትና እኛ ሕዝበ ክርስቲያን በረከተ ሥጋ ወነፍስ የሚያሰጡ አገልግሎቶች ላይ እንድንሳተፍ ቤተክርስቲያኗ ጥሪ እያደረገች ትገኛለች። ከሁሉ በፊት በጸሎት እንዲያስቡን እየጠየቅን በሃሳብ፣ በጉልበት፣ በገንዘብ ከቤተክርስቲያናችን በረከትን እንዲያገኙ ቢችሉ ወደ ቦታው ድረስ በመምጣት እንዲያዩ፤ ያልቻላችሁ በመደወል አስፈላጊውን መረጃ በሰፊው ማግኘት ትችላላችሁ እንላለን። አሁን ቤተክርስቲያኗ ምን ያስፈልጋታል?

ቤተክርስቲያንን መስራት፡ አሁን ያለችበት ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ በቆርቆሮ የተሰራ ሲሆን ይህም የመጀመሪያዋን ቤተክርስቲያን ከሸራና ሳጣራ መጠኗ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ቆርቆሮ በቆርቆሮ ለብሳለች ፤ እንዲሁም ካህናት ቅኔ ማኅሌት የሚቆሙበት፣ ምዕመናን የሚያስቀድሱበትና ክቡር ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበት ግድ በመሆኑ ከመቅደሱ ተቀጥሎ በፎቶው ላይ እንደምታዩት ቆርቆሮ የለበሰ ቅኔማኅሌትና ቅድስት ተሰርቷል። ይህ ግን ለዘላቂው የሚሆን ሳይሆን ለጊዜው ለአገልግሎቱ ተብሎ ሲሆን ለዘላቂው ግን ቋሚ ቤተክርስቲያን መስራቱ ግድ ነው። ይህንንም የደብሩ ሕንፃ አሰሪ ኮሚቴ አስፈላጊውን እያደረገ ሲሆን እርሶም ይህ ሕንፃ ቤተክርስቲያን በመልካም ተጀምሮ እንዲፈጸም በጸሎቶ ያስቡን። እንዲሁም ለቤተክርስቲያኗ ማሰሪያ ይሆን ዘንድ በማቴርያል ወይም በገንዘብ ለቤተክርስቲያኗ በደረሰኝ መስጠት እንደምትችሉ እና ከበረከቱ እንድትሳተፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።



ለበሻሌ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ሕንፃ ግንባታ የሚያስፈልጉ
1
ሲሚንቶ
340 ኩንታል
2
አሸዋ
79 ሜትር ኩብ
3
ጠጠር
46 ሜትር ኩብ
4
ድንጋይ
30 ሜትር ኩብ
5
ብሎኬት
2592 በቁጥር
6
የብረት መስኮት
1.8 x 4.75 (8.55 ካሬ)= 3 በቁጥር


0.9 x2.5 (2.25ካሬ) =10 በቁጥር


0.8 x1.9 (1.52ካሬ)= 7 በቁጥር


1.2 x1.4 (1.68ካሬ) =3 በቁጥር
7
መስታወት
76 ካሬ ሜትር

1. ቀለም ስራ እስቱኮ
36 ኪሎ

2. ግሎ
8 ኪሎ

3. ቀለም
112 ሊትር

4. ጂፕሰም
18 ኪሎግራም
8
የእንጨት በር
0.9 x2.5= 3በቁጥር

1.2 x2.6
1በቁጥር
9
ቆርቆሮ ጣሪያ
252 በቁጥር
10
አሸንዳ
90 ሜትር
11
1. ባህር ዛፍ አጠና (10-12)
20 በቁጥር

2. ምስማር
5 ኪሎግራም
12
ባህር ዛፍ ውቅረት


1. አጠና (8-10)
32 በቁጥር

2. ምስማር
7ኪሎግራም

3. ሞራሌ (5x7)
37 በቁጥር

4. ምስማር
3 ኪሎግራም
13
ከፈፍ ጣውላ


1. ጣውላ
36 በቁጥር

2. ምስማር
12 ኪሎግራም
14
ኮርኒስ


1. ሞራሌ(5x5)
300

2. ቺፕውድ
280 ካሬ ሜትር 100 በቁጥር

3. ምስማር(6 cm)
18 ኪሎግራም

4. ምስማር (3cm)
18 ኪሎግራም
15
ወለል
ሊሾ 225 ሜትር ካሬ
16
ቶንዲኖ ብረት (ፌሮ)
6 =136 ኪሎግራም


8= 442 ቤርጋ


10= 4 ቤርጋ


12 =132 ቤርጋ


14= 49 ቤርጋ


16= 38 ቤርጋ


20=12 ቤርጋ

ለበለጠ መረጃ ስልክ፡ 0911563714 (መልዓከ ፀሐይ ሲራክ የቤተክርስቲያኗ ዋና አስተዳዳሪ) ይደውሉ።

“በኃይልህ ሰላም፥ በጌጠኛ ቤትህም ልማት ይሁን።”
መዝ. 122፡7
ምንጭ፡ የደብረ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ጽ/ቤት ታሕሳስ 1/ 2004 ዓ.ም