20111221

ታላቅ ዜና ቤተክርስቲያን

“ቤተ መቅደስህ ቅዱስ ነው በጽድቅም ድንቅ ነው።” መዝ. 65፡ 5

ቀዳማዊ ዜና
የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን

በንብ የሚጠበቀው የቦሌ በሻሌ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወአቡነ ሠላማ ቤተክርስቲያን በሕዳር 12 / 2002 ዓ.ም ለሚከበረው የቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በዋዜማው ሕዳር 11 ቀን ዋዜማ ቆመው ሳለ ከምስራቅ አቅጣጫ አውራውን አስቀድሞ እየተመመ የመጣው የንብ መንጋ ቤተክርስቲያኗን ዞሮ ጣራዋ ሸራ ግድግዳዋ ሳጠራ ወደሆነችው ቤተመቅደሷ ብቻ በተሰራው (ቅድስት እና ቅኔ ማኅሌት የሌለው አነስተኛ መጠን ያላታ ቤተክርስቲያን ላይ) የቃልኪዳኑ ታቦተ ሕግ ባረፈበት መንበር ውስጥ መንጋው ንብ ገብቶ ሰፍሯል። የንቡ መንጋ ወደ መንበሩ ሲገባ በአገልግሎት ላይ ያሉትን ካህናት ሳይነካ አገልግሎቱም ሳይታጎል አድሯል። በሕዳር 12 ምንም እንኳን ካህናቱ ስጋት ቢገባቸውም ታቦተ ሕጉን ማውጣት ግዴታ ነውና አስፈላጊውን ስርዓተ አምልኮ ከተፈፀመ በኋላ ታቦተ ሕጉ ከመንበረ ክብሩ ሲወጣ የንቡም ሠራዊት ከመንበሩ በምስራቅ በኩል ወተው አንድም ምዕመን ሳይነድፉ አብረው ከታቦቱ ጋር አክብረው ወደ መንበሩ ሰፍረዋል። አሁንም በመንበሩ ውስጥ ይገኛሉ። የመንበር ውስጥ ማርም ማኅበረ ምዕመናኑ እየበላ ከቅዳሴ ፀበሉ ጋር እየጠጣ ድኅነተ ሥጋና ድኅነተ ነፍስን እያገኙ ይገኛሉ።
ሊቃውንት ይህን ተዓምር ሲተረጉሙ፡ ንቡ ሠራዊተ መላእክት (ነገደ ቅዱስ ሚካኤል) ናቸው ብለው በዕለቱ አስተምረውናል ይህም በተግባራቸው የተገለጸ ነውና እንደምን ቢሉ ከቀናት ተመርጦ በሕዳር 12 ዋዜማ መምጣታቸው ሕዳር 12 ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ተብሎ የተሾመበት እስራኤላውያንን ከግዞት አውጥቶ በምድረበዳ የመራበት መናን ያዘነበበት መታሰቢያ ዕለት ነውና በበዓለ ሲመቱ ክቡራን ንዑዳን የሚሆኑ ሠራዊተ መላዕክት በምስራቅ በኩል በምትገኘው በስተምስራቅ በኩል ስብሐተ እግዚአብሔር በሚደርስበት ሰዓት መተዋልና ነው። አንድም በአካባቢው የተለያዩ ዛፎች እንዲሁም መኖሪያ ቤቶች ሳሉ በዚህች ቅድስት ቤተመቅደስ ውስጥ የቅዱስ ሚካኤል እና የቅዱስ እስጢፋኖስ ታቦተ ሕግ ባለበት መግባታቸው ሠራዊተ መላእክት ናቸው በማለት ተዓምሩን ተርጉመዋል።
አዲስ ዜና
በሕዳር (ልብ ይበሉ ሁለቱም ታላላቅ ዜናዎች የተፈጸሙባቸው ወር አንድ ናቸው “ወርሐ ሕዳር”) በሕዳር 21 ቀን 2004 ዓ.ም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ የሆነችው ታቦተ ጽዮን ዳጎንን ድል አድርጋ በክብር የተመለሰችበትን በዓል በሚከበርበት ዕለት ካህናት በሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ሳሉ ከየት መጣ ተብሎ የማይታወቅ እጅግ ብዙ የሆነ የንብ መንጋ ዳግም ወደዚህች ቤተክርስቲያን መጣ። ድምፁ ያስደነገጣቸው ቀዳስያን ካህናት እና ምዕመናን (በቁጥር እጅግ ጥቂት የሆኑ) ምን መጣ? ወይስ የመንበሩ ንቦች ወጡን? በማለት ሲደናገጡ ከዲያቆናት መካከል አንዱ ወጥቶ ቢመለከት በጉልላቱ ስር የመስቀል ምልክት ሰርተው በጣራው ላይ ብዙሃኑ ሲያርፉ የቀረው ቤተክርስቲያኗን ይዞራል። “በልዎ ለእግዚአብሔር ግሩም ግብርከ፡ እግዚአብሔርን ስራህ ድንቅ ነው በሉት” እንዳለ እጹብ ከማለት በቀር ምን ማለት ይቻላል? ይህም የንብ ሠራዊት ሥርዓተ ቅዳሴው ሲያበቃ አዲስ በተሰራችው፣ በመጠኗ አነስተኛ የሆነውችው ቤተልሔም ውስጥ ገብቶ ሰፍሮ ይገኛል። ከደብሩ አገልጋይ ካህናት ውስጥ አንዱ ቄስ ገብተው ሲያጥኑና የንቡን ሁኔታ ሲመለከቱ ከመግባቱ ገና በ10ኛ ቀኑ ማር ለመስራት የሚያስፈልገውን የመጀመሪያ ደረጃ እንደጀመረ የደብሩ አስተዳዳሪ መልዓከ ፀሐይ ሲራክ ገበየሁ በታሕሳስ 1 ቀን 2004 ዓ.ም በተዘጋጀው ልዩ መርሐ ግብር ላይ ለምዕመናን ተናግረዋል።
በደብሩ እየተደረጉ ካሉ ተዓምራት ውስጥ ለአብነት ያህል፡
v በከባድ የራስ ምታት በሽታ (ማይግሬን) ለ15 ዓመታት ሲሰቃዩ የነበሩ አንድ ምዕመን ከመንበሩ ውስጥ በወጣችው አንድ ንብ ራሳቸውን ተነድፈው ድነዋል።
v በእብድ ውሻ ተነድፎ ይሰቃይ የነበረ ምዕመን በህክምና ማዕከል የውሻውን አንገት ካላመጣህ ልትድን አትችልም ተብሎ እየተሰቃየ የነበረ በቦታው መጥቶ በሁለት ንቦች የተነከሰበት ቦታ ተነድፎ ከበሽታው ሙሉ በሙሉ ድኗል።
v አንዲት ምዕመን ለ5 ዓመታት ያህል በአእምሮ በሽታ አብዳ ቤተሰቦቿን የማታውቅ የነበረች ከማሩ ጸበል ወስደው ቢያጠጧት በ5ኛው ቀን ድና ምስክርነት ሰጥታለች።
v በኪንታሮት በሽታ ለብዙ ዘመናት ሲሰቃይ የነበሩ ምዕመን ከመንበሩ የተቆረጠውን ማር ተቀብተው ድነዋል።
v ለብዙ ጊዜ መስማት ተስኖት የነበረ ምዕመን ማሩን በጥብጦ በጆሮው ውስጥ ቢከት ወዲያው ድኖ መስማት ችሏል።
v እጅና እግሯ ሲንቀጠቀጥ የነበረች ሴት በፀሎት ላይ ሳለች በአንድ ንብ ተነድፋ ወዲያውኑ ከበሽታዋ ድናለች።
v በአስም፣ በጨጓራ፣ በኩላሊት፣ በደም ግፊት፣ በጭንቀት በሽታ ሲሰቃዩ የነበሩ ምዕመናንም ማሩን ጠጥተው፤ ከመንበሩ በሚወጡ ንቦች ተነድፈው ድነው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

“ምንተ ንግበር አሀዊነ፡ ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ።” (ሐዋ. 2፡ 37)
ይህች ቅድሰት ቤተክርስቲያን እጅግ ብዙ የሆነ ገቢረ ተዓምራትን እያደረገች የምትገኝ የሠማይ ደጅ ናትና ገና ብዙ ምዕመናን ድኅነተ ሥጋንና ድኅነተ ነፍስን የሚያገኝባት ናትና እኛ ሕዝበ ክርስቲያን በረከተ ሥጋ ወነፍስ የሚያሰጡ አገልግሎቶች ላይ እንድንሳተፍ ቤተክርስቲያኗ ጥሪ እያደረገች ትገኛለች። ከሁሉ በፊት በጸሎት እንዲያስቡን እየጠየቅን በሃሳብ፣ በጉልበት፣ በገንዘብ ከቤተክርስቲያናችን በረከትን እንዲያገኙ ቢችሉ ወደ ቦታው ድረስ በመምጣት እንዲያዩ፤ ያልቻላችሁ በመደወል አስፈላጊውን መረጃ በሰፊው ማግኘት ትችላላችሁ እንላለን። አሁን ቤተክርስቲያኗ ምን ያስፈልጋታል?

ቤተክርስቲያንን መስራት፡ አሁን ያለችበት ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ በቆርቆሮ የተሰራ ሲሆን ይህም የመጀመሪያዋን ቤተክርስቲያን ከሸራና ሳጣራ መጠኗ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ቆርቆሮ በቆርቆሮ ለብሳለች ፤ እንዲሁም ካህናት ቅኔ ማኅሌት የሚቆሙበት፣ ምዕመናን የሚያስቀድሱበትና ክቡር ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበት ግድ በመሆኑ ከመቅደሱ ተቀጥሎ በፎቶው ላይ እንደምታዩት ቆርቆሮ የለበሰ ቅኔማኅሌትና ቅድስት ተሰርቷል። ይህ ግን ለዘላቂው የሚሆን ሳይሆን ለጊዜው ለአገልግሎቱ ተብሎ ሲሆን ለዘላቂው ግን ቋሚ ቤተክርስቲያን መስራቱ ግድ ነው። ይህንንም የደብሩ ሕንፃ አሰሪ ኮሚቴ አስፈላጊውን እያደረገ ሲሆን እርሶም ይህ ሕንፃ ቤተክርስቲያን በመልካም ተጀምሮ እንዲፈጸም በጸሎቶ ያስቡን። እንዲሁም ለቤተክርስቲያኗ ማሰሪያ ይሆን ዘንድ በማቴርያል ወይም በገንዘብ ለቤተክርስቲያኗ በደረሰኝ መስጠት እንደምትችሉ እና ከበረከቱ እንድትሳተፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።



ለበሻሌ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ሕንፃ ግንባታ የሚያስፈልጉ
1
ሲሚንቶ
340 ኩንታል
2
አሸዋ
79 ሜትር ኩብ
3
ጠጠር
46 ሜትር ኩብ
4
ድንጋይ
30 ሜትር ኩብ
5
ብሎኬት
2592 በቁጥር
6
የብረት መስኮት
1.8 x 4.75 (8.55 ካሬ)= 3 በቁጥር


0.9 x2.5 (2.25ካሬ) =10 በቁጥር


0.8 x1.9 (1.52ካሬ)= 7 በቁጥር


1.2 x1.4 (1.68ካሬ) =3 በቁጥር
7
መስታወት
76 ካሬ ሜትር

1. ቀለም ስራ እስቱኮ
36 ኪሎ

2. ግሎ
8 ኪሎ

3. ቀለም
112 ሊትር

4. ጂፕሰም
18 ኪሎግራም
8
የእንጨት በር
0.9 x2.5= 3በቁጥር

1.2 x2.6
1በቁጥር
9
ቆርቆሮ ጣሪያ
252 በቁጥር
10
አሸንዳ
90 ሜትር
11
1. ባህር ዛፍ አጠና (10-12)
20 በቁጥር

2. ምስማር
5 ኪሎግራም
12
ባህር ዛፍ ውቅረት


1. አጠና (8-10)
32 በቁጥር

2. ምስማር
7ኪሎግራም

3. ሞራሌ (5x7)
37 በቁጥር

4. ምስማር
3 ኪሎግራም
13
ከፈፍ ጣውላ


1. ጣውላ
36 በቁጥር

2. ምስማር
12 ኪሎግራም
14
ኮርኒስ


1. ሞራሌ(5x5)
300

2. ቺፕውድ
280 ካሬ ሜትር 100 በቁጥር

3. ምስማር(6 cm)
18 ኪሎግራም

4. ምስማር (3cm)
18 ኪሎግራም
15
ወለል
ሊሾ 225 ሜትር ካሬ
16
ቶንዲኖ ብረት (ፌሮ)
6 =136 ኪሎግራም


8= 442 ቤርጋ


10= 4 ቤርጋ


12 =132 ቤርጋ


14= 49 ቤርጋ


16= 38 ቤርጋ


20=12 ቤርጋ

ለበለጠ መረጃ ስልክ፡ 0911563714 (መልዓከ ፀሐይ ሲራክ የቤተክርስቲያኗ ዋና አስተዳዳሪ) ይደውሉ።

“በኃይልህ ሰላም፥ በጌጠኛ ቤትህም ልማት ይሁን።”
መዝ. 122፡7
ምንጭ፡ የደብረ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ጽ/ቤት ታሕሳስ 1/ 2004 ዓ.ም

20111220

ታላቁ ጸድቅ አቡነ ሃብተ ማሪያም


ታላቁ ጸድቅ አቡነ ሃብተ ማሪያም ከተከበሩና ህገ እግዚአብሔር ጠብቀው በትሩፋት ከሚተጉ በንጽህናና በቅድስና ይኖሩ ከነበሩ አባታቸው ፍሬ ብሩክ ከ እናታቸው ዮስቴና ከተባሉ በመንዝ አዉራንጃ ልዩ ስሙ የራዊ በተባለ ቦታ ተወለዱ።

እናታቸው የምነና ሃሳብን ለመፈጸም ወደ አንድ ገዳም በሚሄዱበት ወቅት አንድ መነኩሴ "ምንኩስና ለአንቺ አልተፈቀደም ወደ ቤትሽ ግቢ ጸሎቱ ዓለም ሁሉ የሚጠቅም ሰዉ ሁሉ የሚማጸነው ስሙ ገድሉ ትሩፋቱ በዓለም ሁሉ የሚነገርለት በአፀደ ስጋ በአፀደ ነፍስ የሚያማልድ በምድር ሆኖ መንበረ ጸባኦትን የሚያይ ወንድ ልጅትወልጃለሽ " ባላቸው መሰረት የተወለዱና በእናታቸው ጀርባ ታዝለው ክህኑ በቤተክርስትያን "እግዚኦ ማሀረነ ክርስቶስ" ሲል በህፃን አንደበታቸው "እግዚኦ ማሀረነ ክርስቶስ"ይሉ ነበር ።

ባደጉ ጊዜ ትምህርታቸዉን ከጥሩ ስነ ምግባርና ህግን ከመጠበቅ ጋር ጠንቅቀው ከመማር ባሻገር በ አባ ሳሙሄል እጅ ምንኩስናን ተቀብለዋል።
ከአቡነ መልከ ፃዲቅ ገዳም ተነስተው ሲሄዱ መንገድ ላይ ከ አንድ ዋሻ ዉስጥ ለ ሶስት ወራት በ ጸሎት ቆይተዋል እግዚአብሔር "መታሰቢያህን በዚህ ዋሻ አደርገውዋለዉ" ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል ።
ይህ ዋሻ ዩሰበይ አባ ሃብተ ማሪያም ገዳም በመባል ይታወቃል . ከደብረ ሊባኖስ ዝቅ ብሎ በእግር 2ሰዓት መንገድ ላይ ያለዉ ን በሰበይ የተባለዉንም ገዳም በስማቸው መሰረቱት ፅንሰታቸው ነህሴ 26 ልደታቸው ግንቦት 26 ነ እረፍታቸው ኅዳር 26 ቀን ነው የፃድቁ አባታቺን የአቡነ ሃብተማሪያም ጸሎት እና አማላጅነት በሁላችን ላይ አድሮ ይኑር ።

አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ


አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ ሀገራቸው ንሂሳ (ግብጽ ) ነው :: አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌያስ ይባላሉ :: ልጅ አጥተው 30 ዘመን ሲያዝኑ ኖረዋል ::
አንድ ቀን አቅለያስ ቤተ እግዚአብሔር ገብታ ከስዕለ ስላሴ ስር ወድቃ ስትማጸን "" ንስኢ ወልደ ዘይትሌአል ቅርኑ አምኑኅ ሰማይ ... ክብሩ ከሰማይ ከፍታ የሚበልጥ ልጅ እንኪ ተቀበዪ "" የሚል ድምጽ ሰማች :: በዚህም መሰረት አባታችን መጋቢት 29 ቀን ተጸንሰው ታህሳስ 29 ቀን ተወለዱ ::

አይን በገለጹ ጊዜ ከሚታይ ነገር ላይ እንዲያርፍ እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ አፈፍ ብለው ተነስተው "" ስብሐት ለአብ , ስብሐት ለወልድ , ስብሐት ለመንፈስቅዱስ ዘአውጻእከኒ እምጽልመት ውስተ ብርሐን >> ብለው በማመስገናቸውና ቡሀላም ምድራዊ መብል እና መጠጥ ሳይመገቡ : ሳይጠጡ ለምስጋና ተግተው በመኖራቸው መልአክትን ይመስላሉ

ሶስት አመት ሲሆናቸው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእመቤታችንና በገነት ካሉ ቅዱሳን ዘንድ አስባርኮ ገዳማውያን ካሉበት ምኔት ወስዶ ከበሩ አኖራቸው :: አበመኔቱም አባ ዘመድብርሐን ምልክት ተነግሮት ቢሄድ ፍሱሐ ገጽ ሆነ አግኝተዋቸዋል :: አበመኔቱም አሳድጎ አስተምሮ ከመአረገ ምንኩስና አድርሰዋቸዋል ::

ከዚህ ቡሐላ ሐብተ ፈውስ ተሰጥቷቸውል :: በአንድ ቀን እልፍ እውራንን እና እልፍ አንካሳ ፈውሰዋል :: በዋላ ግን ኤጲስ ቆጶሳትና ካህናቱ ዝናቸውን ሰምተው እየመጡ ግብር የሚያስፈቱአቸው ቢሆን ቅዱስ ገብርኤል ነጥቆ ከጌታ ፊት አቀረባቸው ::

በገድለህ : በትሩፋትህ : ከሞት ነፍስ ክርደት ገሀነም የሚድኑ ብዙ አሉና ከሰው ተለይተህ ወደ ጫካ ግባ :: ኑሮህም ከስልሳ አናብስትና ከስልሳ አናብርት ጋር ይሁን አለው :: ጌታዬ ምን ተመግበው ይኖራሉ አሉት ? "ዘኬድከ ጸበለ - እግረከ ይልህሱ ወበ ውእቱ ይጽግቡ ... የረገጥከውን ትቢያ ልሰው ያ ምግብ ሆኗቸው ይኖራሉ :: ብሏቸው ውሳጤ ገዳም ገብተው : ከአናብስትና ከአናብርት ጋር ይኖሩ ጀመሩ :: ዳንኤል ከአናብስት ጉድጉዋድ በተጣለ ጊዜ አናብስቱ እንደ ድመት ከእግሩ በታች ሆነው እንደተገኙ : አባታችን የረገጡትን ትቢያ እየላሱ እየታዘዙዋቸው ይኖሩ ነበር :

በዚህ መልኩ 30 አመት ከቆዩ ቡሐላ ጌታ በአንድነት በሶስትነት ተገልጾ ምን ላደርግልህ ትሻለህ ? አላቸው :: መጀመሪያ ላሉበት መጸለይ ይገባልና የምድር ገቦታን ሰዎች ማርልኝ አሉት :: 3000 ሐጥአንን ከሲኦል አውጥቶ ገነት አግብቶላቸዋል :: ከዚህ ቡሐላ ሁር ምድረ ኢትዮጵያ ወበህኒ አልውከ ነፍሳት ወታወጽኦሙ .... ወደ ኢትዮጵያ ሂድ አላቸው :: ቅዱስ ገብርኤል በሰረገላ ነፍስ ጭኖ ምድረ ከብድ አድርሷቸዋል :: ዳግመኛም ወደ ዝቁዋላ (ደብረቅዱስ ) ወስዷቸው ከዚያ ሆነው በንጹሀ ልቦና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሐጢያት ከባህሩ ውስጥ ራሳቸውን ዘቅዝቀው ለ 100 አመት ይጽልዩ ነበር :: 40 ቀን ሲሆናቸው መልአኩ መጥቶ ዘገብረ ተዝካርከ ወዘጽውአ ስምከ እምህር ለከ ብሎሀል አላቸው :: እሳቸው ግን መላ ኢትዮጵያን ካልማረልኝ ከባህሩ አልወጣም ብለው 100 አመት በባህሩ ውስጥ በጭንቅላታቸው ተዘቅዝቀው ሲጸልዩ ኖረዋል :: ከ 100 አመት ቡሐላ ጌታ ተንስእ ወጽእ መሀርኩ ለከ ኩሎ ኢትዮጵያ ... ምሬልሀለው ውጣ ብሏቸው ወጥተዋል ::

ከዚህ ቡሐላ ምድረ ከብድ ወርደው ከምድር በላይ ከሰማይ በታች ሆነው 7አመት እንደ ትኩል አምድ ሆነው አይናቸውን ሳይከድኑ 7 አመት ሙሉ አይናቸውን ሳይከድኑ ቆመው ጸልየዋል :: ሰይጣን ግን ለምቀኝነት አያርፍምና ቁራ መስሎ መጥቶ አይናቸውን አንቁሮ አሳወራቸው :: 2 ሱባኤ ሲፈጽሙ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል መጥተው እፍፍ ብለው አድነዋቸዋል :: ከዚያ ተነስተው ወደ ዝቁዋላ ሲሄዱ ስላሴን በአምሳሌ አረጋውያን ከጥላው ስር አርፈው አገኙዋቸው :: በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጽነንሀል አዝለክ አንድ አንድ ምህራፍ ሸኘን አሉዋቸው :: አዝለው ከሸኙዋቸው ቡሐላ በአንድነት በሶስትነት ሆኖ ታያቸው :: ድንግጠው ወደቁ : እግዚአብሔር ግን አንስቷቸው ሂድ ዝቁዋላ ሄደህ ጠላቶችህን ተበቀላቸው አላቸው :: በዛበነ መብረቅ ደርሰው 7 ቱን ሊቃነ መላእክት አጋዥ አድርገው እልፍ አእላፍ አጋንንትን አጭደዋል ::

የቅዱስ ሚካኤል ስሞች




መላእክት ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ቢሆንም በ99 ነገድ የተከፈሉና አለቆችም ያሏቸው ናቸው፡፡ የእነዚህ ሁሉ መላእክት አለቃ የሆነው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ በትህትናው ልዕልናን ያገኘው ቅዱስ ሚካኤል በእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠው ክብር ከማንኛውም መልአክ የበለጠ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡

ሚካኤል ማለት ‹ከመ እግዚአብሔር እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው; ማለት ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ገናንነትና እሱን የሚመስል አምላክ እንደሌለ የሚያመለክት ነው እንደ እግዚአብሔር ያለ ቅዱስ ንጹሕ ርህሩህ ኃይል ረቂቅ ማነው መልሱ የለም ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል የስሙ ዘርፍ ሆነው የሚጨመሩ መጠሪያዎች አሉት እነዚህም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠውን የባለሟልነት ክብር የሚገልጹ ናቸው፡፡ ይኸውም መልአከ ኃይል$ መጋቤ ብሉይ$ መልአከ ምክሩ…ናቸው፡፡ መልአከ ኃይል የተባለው እግዚአብሔር በሱ አማካይነት ታላላቅ ሥራዎችን በመሥራት ኃይሉን ስለገለጸ$ ዲያብሎስን ከነሠራዊቱ ስላሸነፈ ነው፡፡ መጋቤ ብሉይ የተባለበት ምክንያት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከእግዚአብሔር እየተላከ ብዙ ታላላቅ ሥራዎችን የሠራ በመሆኑ ነው፡፡

መልአከ ምክር ወይም የእግዚአብሔር የምክሩ አበጋዝ የተባለበት ምክንያት እግዚአብሔርን በምክሩ ይረዳዋል ለማለት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ ለወዳጁ ለቅዱስ ሚካኤል ይገልጽለታል በሱም አማካኝነት ይሠራል ለማለት ነው፡፡

ቅዱስ ሚካኤል በመጽሐፍ ቅዱስ

ቅዱስ ሚካኤል በዚህ ሁሉ ልዕልና ላይ ትሕትናን ደርቦ የያዘ በጸሎቱ ተማጽኖ በተራዳኢነት አምኖ ለሚለምነው ሁሉ ፈጥኖ በመድረስ ከሠራዊተ አጋንንት ተንኰል የሚያድን መልአክ ነው፡፡ ወደ ቅዱስ መጽሐፍ ስንገባ ለቅዱስ ሚካኤል የተሰጠውን ክብርና ባለሟልነት እንዲሁም የሠራቸውን ሥራዎች እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ (ኢያሱ 5$13-15) እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹እንዲህም ሆነ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፡፡ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፡፡ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን አለው፡፡ እርሱም አይደለሁም እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቻለሁ አለ፡፡ ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደ፡፡ ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድን ነው አለው፡፡ የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን አንተ የቆምህበት ሥፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው፡፡ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ ይላል፡፡ ይህን ጥቅስ ልብ ብለን ብናጤነው ለሌላው ሁሉ መርህ ይሆናልና ጥቂት ለማብራራት እንሞክራለን፡፡

እንዲሁም እግዚአብሔር ራሱ ለኢያሱ ‹‹…በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም ከሙሴ ጋር እንደሆነው እንዲሁ ካንተ ጋር እሆናለሁ አልጥልህም አልተውህም፡፡…›› (ኢያሱ 1$1-9) በማለት ምን ያህል እንዳከበረው ያስረዳል፡፡ እስራኤላውያን አሞራውያንን በወጉ ጊዜ ቀኑ ስለመሸባቸው ከመደበኛው የተፈጥሮ ሕግ ውጭ ቀኑ እንደማይጨልምና መዓልቱ እንዲረዝም ኢያሱ በጸሎት ፈጣሪውን ስለጠየቀ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ቀኑን አስረዝሞ ከሰማይ በረድ አዝንሞ ጠላቶቻቸውን በማጥፋት የፈጸመውን አስደናቂ ተአምር እንዲህ ብሎ ጸፏል፡፡

‹‹...ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል (ልመና) የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም›› (ኢያ 10$12-14) በማለት ተገልጿል፡፡ በጠቅላላው ከኢያሪኮ ጀምሮ ታላላቅ የአሕዛብ ምሽጐችን አፍርሶ አሕዛብን አጥፍቶ እግዚአብሔር ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብ የማለላቸውን የተስፋይቱን ምድር ለልጆቻቸው ያወረሰ ኢያሱ ነው፡፡

ይህ የእስራኤል መሪ በእጅ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ የተገለጸለት ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን አላወቀም፡፡ ከቃሉ እንደምንረዳው ከራሱ ወገን ወይም ከጠላቶቹ ወገን የሆነ አንድ ወታደር መስሎት ነበር፡፡ መልአኩ በሰው አምሳል ስለተገለጸለት አላወቀውም ነበር፡፡ ያነጋገረውም ያለ ፍርሃት ያለ ጭንቀት ያለድንጋጤ ወታደሮቹን እንደሚያነጋግር ዘና ብሎ ነው፡፡ ሆኖም ከመልአኩ የተሰጠው መልስ ታላቅ መሪና ነቢይ የሆነውን የኢያሱን አስተሳሰብ ለወጠው፡፡ ይኸውም ‹‹ከወገኖችህ ወይም ከጠላቶችህ አይደለሁም እኔ አሁን መጥቻለሁ$ የሚለውን ቃል ሲሰማ ኢያሱ በፊቱ የቆመው ተራ ወታደር ሳይሆን የመላእክት ሠራዊት አለቃ ከሙሴ ሳይለይ የእስራኤልን ሕዝብ የሚጠብቅ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን ሲረዳ ለመልአኩ ክብር መስጠት ስለሚገባ የአክብሮት ስግደት ሰገደለት›› #ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድነው;$ በማለት በትህትና ጠየቀ፡፡ ጌታዬ አንተ ቅዱስ ሚካኤል ለኔ ለባሪያህ ለኢያሱ የምትነግረኝ ምንድነው; በማለቱ የእግዚአብሔርን ክብር ለፍጡር መስጠቱ አይደለም መላእክት ጌቶች ይባላሉ፡፡ ጌትነታቸውም የጸጋ ጌትነት ነው፡፡

ኢያሱ መልአኩን ጌታዬ ብሎ ከጠራው እኛማ ኃጢአተኞች ጌታዬ፤ ቀዱስ ሚካኤል ለኔ ለባሪያህ ጸልይልኝ መጥተህ አድነኝ…በማለት የአክብሮት (የጸጋ) ስግደት በመስገድ ብንለምነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውጭ አልወጣንም፡፡ የፈጣሪን ክብር ለፍጡር አልሰጠንም፡፡ ተሳስታችኋል የሚለን ሰው ቢኖር እኛ አብነት ያደረግነው የእግዚአብሔር ወዳጅ ኢያሱን ስለሆነ ኢያሱም ተሳስተሃል ይባል፡፡ መልአኩም ኢያሱ ያቀረበለትን የአክብሮት ስግደትና ጥያቄ በመቀበል ከእግዚአብሔር የተሰጠውን መልእክት ነገረው፡፡ ኢያሱም ትእዛዙን ፈጸመ፡፡

እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ማለት መላእክትን ፈጥሮ የሚገዛ፣ የሚያዛቸው፣ የሚቀድሳቸው ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ የሚለው ከፈጣሪ በታች በመላእክት ላይ በፈጣሪ የተሾመ ማለት ነው፡፡ መላእክት አለቆቻቸውን ያከብራሉ፤ ለእነሱም ይታዘዛሉ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት ሁሉ አለቃ ስለሆነ ከትእዛዙ አይወጡም፤ ሠራዊተ መላእክት የሚያከብሩትንና የሚታዘዙለትን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን እኛም እንደ ኢያሱ እናከብረዋለን እንታዘዘዋለን፡፡ መላእክትን ማክበርና መታዘዝ እንደሚገባ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡፡ #በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክህን በፊትህ እሰዳለሁ፤ በፊቱ ተጠንቀቁ፤ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት፤ አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፣ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፣ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፣ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ፣ መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና…$(ዘጸ.23$2ዐ-22) በማለት ለሙሴ ተናግ ል፡፡ ይህ ቃል ለአንድ ጊዜ ብቻ ለሙሴና ለሕዝቡ ተነግሮ ያበቃ ሳይሆን እስከዛሬና ወደፊትም የሚቀጥል ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ያን ጊዜ ሕዝበ እስራኤልን ፊት ፊት እየመራ ጠላቶቻቸው አሕዛብን አጥፍቶ ምድረ ርስትን ምድራዊት ኢየሩሳሌምን እንዳወረሳቸው ዛሬም ይኸው መልአክ ቅዱስ ማካኤል እስራኤል ዘነፍስ የተባልን ህዝበ ክርስቲያንን ፊት ፊት እየመራ ጠላቶቻችን ሠራዋተ አጋንንትን እያጠፋ ምድረ ርስት ወደተባለች ሰማየ ሰማያት ያገባናል፡፡ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ለአዲስ ኪዳን ሕዝብ ምሳሌ ስለሆነ በታሪክነቱ ብቻ ተነግሮ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ኦሪት ሰም ሲሆን ሐዲስ ኪዳን ደግሞ ወርቅ ነውና፡፡

ይህ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ያወጣ፣ በበረሃ 4ዐ ዓመት የመራቸው፣ ምድር ርስትን ያወረሳቸው መሆኑን በሌላ ስፍራ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹…በእስራኤል ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፊቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፡፡›› (ዘጸ.14$15-20) በዚህ መሠረት እስራኤልን ይመራ የነበረው የእዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ እንዲሁም በኮሬብ ተራራ እግዚአብሔር ለሙሴ ሐመልማል ከነበልባል ተዋሕዶ በተገለጸለት ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አልተለየም ነበር፡፡ (ዘጸ.3$1-6፣ የሐዋ. 7$3ዐ-34) በኦሪት የእግዚአብሔር መልአክ እየተባለ የሚጠራው አብዛኛውን ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ በድርሳነ ሚካኤልም ተጽፎ ይገኛል፡፡ (መዝ.33$7) ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ (ቅዱስ ሚካኤል) እግዚአብሔርን በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸዋል (በኢሳ.37$36) ›› የእግዚአብሔር መልአክ(ቅዱስ ሚካኤል) መጣ፡፡ ከአሞራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ…›› በማለት ቅዱስ ሚካኤል ሕዝቅያስን እንዴት እንዳዳነው ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ሚካኤል ያልረዳው ቅዱስ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በዳን.1ዐ$13 ‹‹የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ$ በማለት የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ተገልጿል /ዳን.1ዐ$21/፡፡ በዚሁ በትንቢተ ዳንኤል ም.12$1 ላይ ‹‹በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል በማለት ታላቅነቱን፤ለሰው ልጆች ሁሉ በአማላጅነቱና በተራዳኢነት የሚቆም እንደሆነ በማያሻማ ቃል ተገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ ዲያብሎስ ከነሠራዊቱ በእግዚአብሔር ላይ ባመፀ ጊዜ ከክብሩ ያዋረደው ወደምድር የጣለው ቅዱስ ሚካኤል ቅዱሳን መላእክትን በመምራት ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ ጋር ስላደረገው ጦርነትና ስለተቀዳጀው ድል ቅዱስ ዮሐንስ እንዲሀ በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ፤ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፡፡ አልቻላቸውምም፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም፡፡ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው፡፡ ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀድሞው እባብ ወደ ምድር ተጣለ፡፡ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ…$ (ራእ.12$7-9) ዛሬም ቅዱስ ሚካኤል ሰዳዴ አጋንት አጋንንትን የሚያሳድድ በመሆኑ ከሰይጣንና ከሠራዊቱ መከራ እንዲያድናቸው በጸሎት ለሚለምኑት በቃል ኪዳኑ ለሚማፀኑት ሁሉ ፈጥኖ እየደረሰ ይታደጋቸዋል፡፡ በዙሪያቸው እየከተመ አጥር ቅጥር ሆኖ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድናቸዋል (መዝ.33$7)፡፡

በመልእክተ ይሁዳ ቁ.9 ‹‹የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገስጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም$ በማለት ቅዱስ ሚካአል ዲያበሎስን እንኳ እግዚአብሔር ይፍረድብህ ከማለት በቀር ሌላ ቃል አለመናገሩ ታጋሽነቱን ያሳያል፡፡

የቅዱስ ሚካኤል ክብር

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቅዱስ ሚካኤል ለማንም ያልተሰጠ እጅግ ታላቅ የሆነ ክብር እንደተሰጠው ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ይኸውም በዕለተ ምጽአት ጌታችን ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ በክበበ ትስብአት በግርማ መለኮት በሚመጣበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሙታን ላይ ሥልጣን የተሰጠው ለዚሁ ለኃያሉ መልአክ ለቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ በሚገባ ገልጾታል፡፡ እነሆ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ ሁላችን አናንቀላፋም፡፡ ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋል፤ ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን ይላል(1ቆሮ.15$51-52) ከዚሁ ጋር በተጨማሪ ‹‹በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና በክርስቶስ የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ…›› (1ተሰ..4$15-16) በማለት በዕለተ ምጽአት ምን ያህል ክብርና ጌትነት እንደሚሰጠው ይገልጽልናል፡፡

የቅዱስ ሚካኤል በዓል

የቤተ ክርስቲያን አባቶች በየወሩ በ12 መታሰቢያውን እንድናደርግ አዘውናል፡፡ ይህንንም ያልቻለ በዓመት አራት ዐበይት በዓላትን ከቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ጀምሮ እንደተቻለ ማዝከር ይገባል፡፡ እነዚህም ኅዳር 12 ቀን ቀጥሎ ሰኔ 12 ቀን ከዚያም ነሐሴ 12 ቀንና ታኅሳስ 12 ቀን ናቸው፡፡ ከሁሉም የሚበልጠው ታላቁ በዓሉ ኅዳር 12 ቀን ነው፡፡ በዚህም ዕለት እግዚአብሔር በሰማይ ካሉ ሁሉ በላይ አድርጐ ሾመው፡፡ ስለትሕትናውና ስለ መታዘዙ ጌታውን ፈጣሪውን የከዳና የበጐ ሥራ ሁሉ ጠላት የሆነውን ሰይጣንን ድል ይነሣ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው፡፡ በዚህ ዕለት እንዲሁ ከላይ እንደተገለጸው ቅዱስ ሚካኤል በታላቅ ክብር ሆኖ በንጉሥ ጭፍራ አምሳል ለነዌ ልጅ ለኢያሱ የታየበት ዕለት ነው፡፡

በቅዳሴያችን ‹‹ተውህቦ ምሕረት ለሚካኤል፤ ለሚካኤል ምሕረት (ይቅርታ ርኀራኄ) ተሰጠው ይላል፡፡ ነቢዩ ሄኖክም ምሕረት ለሚካኤል መሰጠቱን ገልጿል፡፡ ትሕትናውን ታዛዥነቱን አስረድቷል (ሄኖክ. 6 ቁ.5 ምዕ.10 ቁ.12)፡፡

የሰማያውያን ሠራዊት አለቃ ለሰው ሁሉ የሚራራና ስለ ሰው ልጆች ሳያቋርጥ ወደ ፈጣሪው የሚለምን ርኀሩኀ ትሑት የሆነው ኃያሉ ቅዱስ ሚካኤል የሠራውን ሥራ የክብሩን ገናንነት ጽፈን ለመጨረስ ስለማይቻለን በዚሁ እናበቃለን፡፡ ጸሎቱ እና በረከቱ፣ ተራዳኢነቱም ሀገራችንና ሕዝባችንን ይጠብቅልን አሜን፡፡ (ምንጭ ማህበረ ቅዱሳን )

20110819

“ድንግል ማርያም ” ነኝ ባይዋ ሴት ክስ ሊመሰረትባት ነው

“ የሥላሴ መንፈስ በእኔ ላይ አድሯል፣ ከእግዚአብሔር የተላክሁ ማርያም ነኝ” በሚል ድንኳን በመኖሪያ ቤቷ አካባቢ ተክላ ተከታዮች ስታፈራና እምነቷን ስታስፋፋ የነበረችው ሴት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ እየተካሄደባት ነው፡፡

በአምቦ ከተማ ገላን በተባለ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ተወልዳ በ1994 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ትዕግስት ብርሃኑ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ “ማርያም ነኝ” በሚል ማሳሳቻ ተከታዮችን አፍርታ እንደነበር ከፖሊስ የተገኘ ማስረጃ ይጠቁማል፡፡

በዚሁ አመት የፋሲካ በዓል ሰሞን “እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቼ በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ” በማለት ዝግጅት የጀመረችው ትዕግስት፣ የስቅለት ዕለት የሾህ አክሊልና የምትሰቀልበትን መስቀል አዘጋጅታ ጀርባዋን እንደ ተገረፈች ታውቋል፡፡

በመስቀሉ ላይ መሰቀሏን ያየ ግን አልተገኘም፡፡ በሦስተኛው ቀን ትዕግስት ከሞት ተነሳች ተብሎ ለአካባቢው ህዝብ እንደታየች ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የት ደርሳ እንደመጣች የጠየቃት ስለመኖሩ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡ አብረዋት ይኖሩ የነበሩት አባቷ አቶ ብርሃኑ ድርጊቷን አጥብቀው ይቃወሙ እንደነበር የሚናገሩ ምንጮች ጠጥተው ቤት ሲገቡ በጉዳዩ ይነታረኩ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ አባቷ ግን የልጃቸውን መለኮታዊ ነኝ ባይነት ማስቆም አልቻሉም፡፡ ትዕግስት ይባሱኑ “የሥላሴ መልዕክተኛ ድንግል ማርያም ነኝ” ማለት ጀመረች ይላሉ- ምንጮች፡፡

በዚህ አድሯጎቷ የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ ተቃውሞውን በማሰማት ከአካባቢው አባረራት፡፡ ትዕግስት በዚህ ጊዜ ወንጪ ገዳም እንደገባች የገለፀው ፖሊስ፣ ሀይለገብርዔል ከተባለው ተከታይዋ ሦስተኛ ልጇን እንደወለደች ይናገራል፡፡ ከወንድ ጋር ተገናኝታ እንደማታውቅ የምትናገረው ትዕግስት፣ ሦስቱንም ልጆቼን በመንፈስ ቅዱስ ነው የወለድኳቸው ባይ ናት፡፡ የመጀመሪያ ባለቤቷም ይሄንኑ ይመሰክራል- ከእሷ ጋር ስጋዊ ግንኙነት ፈፅሞ እንደማያውቅና ሁለት ልጆቿን በመንፈስ ቅዱስ እንደወለደቻቸው በመናገር፡፡

ትዕግስት በወንጭ ገዳም ሳለች የሥላሴ መልዕክተኛ ነኝ ማለቷን- ገፍታ ቀጠለችበት፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላ ጉድ መከሰቱን የሚናገሩ ምንጮች፣ እናቷ ወይዘሮ ባይሴ ኡዊሳ (በክርስትና ስማቸው ወለተ ሥላሴ) ነሐሴ 25/2000 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ሞተው እንደተገነዙ፣ ከዚያም የዚያኑ ዕለት ከምሽቱ 4 ሰዓት ከሞት ተነሱ ተብሎ እንደተዋራ ይናገራሉ፡፡ እናት ከሞት የተነሱት ከሰማይ የተላኩትን መልዕክት ለማድረስ እንደሆነ ገልፀው “ወ/ሮ ትዕግስት ወይም በክርስትና ስሟ ምስለ ፍቅር ኢየሱስን ስሟት ተብላችኋል” ካሉ በኋላ በነጋታው ተመልሰው እንደሞቱና ነሐሴ 27/2000 የቀብራቸው ሥነስርዓት እንደተፈፀመ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ግን መቃብራቸው ተከፍቶ እንዳረጉ ነው ልጃቸው ትዕግስት የተናገረችው፡፡

ነሐሴ 29/2000 ዓ.ም ሌሊት ላይ ነጎድጓድ መብረቅ ሰምቶ ከጥበቃ ክፍሉ እንደወጣ የሚናገረው የገዳሙ የጥበቃ ሰራተኛ፣ የትዕግስት እናት መቃብር ላይ መላዕክት እንዳየ ለፖሊስ ገልጿል፡፡ በእጁ አብርቶ ይዞት የነበረው ባትሪ መጥፋቱንና መብረቁ ገፍትሮ እንደጣለው ለፖሊስ የገለፀው የጥበቃ ሠራተኛ በድንጋጤ ወደክፍሉ ተመልሶ እንደገባ ተናግሯል፡፡ ሲነጋጋ ሁኔታውን ለማጣራት ወደ መቃብሩ ሲሄድ የወለተ ሥላሴ መቃብር ለሁለት ተከፍሎና መሃሉ ተሰንጥቆ፣ የአስከሬን ሳጥኑ ባዶ ሆኖ ማየቱን በሰጠው ቃል ገልጿል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ትዕግስት “የዓለም ፍፃሜ ደርሷል፣ ንስሃ ግቡ” እያለች መስበክ መጀመሯን ምንጮች ይናገራሉ፡፡

ሴትየዋ የተቀበሩበት ስፍራ ታጥሮ በሰዎች እየተጎበኘ እንደሆነ የጠቆመው ፖሊስ፣ ሁኔታው የማጣራት ስራ እንደሚፈልግም ይናገራል፡፡

በረቡዕ ቀን በሬና በግ አርዳ ነዋሪዎች በፆም ቀን ሥጋ እንዲበሉ ማስገደዷ ከነዋሪው ጋር ለተፈጠረው ግጭት መንስኤ ሲሆን፣ የፆም ቀን ቢሆንም አብርሃም ቤትም በሬ ተጥሎ ለሰዎች የመገበው ሐምሌ ሰባት እንደሆነ በመፅሃፍ ቅዱስ ተፅፏል በማለት ሐምሌ 7/2002 ዓ.ም ነዋሪው ሥጋ እንዲበላ፣ ካልበሉ ግን ምድር ተከፍታ እንደምትውጣቸው ታስፈራራ ነበር ተብሏል፡፡

ሥጋውን የበላ ይማራል በማለቷ ግማሹ ነዋሪ ቢበላም ግማሹ አልበላም እንዳለ የጠቆሙ ምንጮች፣ በዚህም ምክንያት ትግስት ከአካባቢው ለቅቃ አዲስ አበባ እንደገባች ይናገራሉ፡፡

አዲስ አበባ ከተከታዮቿ አንዷ በሆነችው ሃና ብሩክ በተባለች ግለሰብ መኖሪያ ቤት (ሳር ቤት አካባቢ) ያረፈችው ትዕግስት፣ ከየት እንደመጡ ያልታወቁ 16 ህፃናትና ጎልማሶች አብረዋት ይኖሩ እንደነበር ታውቋል፡፡ ህፃናቱን ለልመና ተግባር ትጠቀምባቸው እንደነበር የጠቆመው ፖሊስ ፣ እሷን ተከታይ እንደሆኑና ደረታቸውን በድንጋይ እንዲደለቁ ታደርጋቸው እነደነበር እንዳረጋገጠ አመልክቷል፡፡

አብዛኞቹ ተከታዮቿ ራሳቸውን የማያውቁና ከትክክለኛ አእምሯቸው እንደተለዩ የሚናገረው ፖሊስ፣ የሴትየዋ ድርጊት የተጋለጠው ህፃናቱ ለጎረቤት “እመብርሃን ናት፣ ደሟን እየቀዳች የክርስቶስ ደም ነው እያለች ታጠጣናለች” ብለው ከተናገሩ በኋላ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በመጠቆም ወ/ሮ ትዕግስት ብርሃኑ በቁጥጥር ስር እንደዋለች ገልጿል፡፡

በወቅቱ ፍተሻ አለመካሄዱን የጠቆመው ፖሊስ፣ ህፃናቱ የት እንዳሉ እንደማያውቅና ምርመራ ላይ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ከሦስት ዓመት በፊት ከተከታዮቿ አንዷ የነበረችው የ19 አመቷ ትዕግስት ያለው ለስምንት ቀን ያለምግብ በመቆየቷ፣ ደረቷን በድንጋይ እንድትደልቅና የተበጠበጠ ምንነቱ ያልታወቀ ቅጠል እንድትጠጣ በመደረጉ ህይወቷ እንዳለፈ ገልጿል፡፡ የወጣቷን አስከሬን በማውጣት የአማሟቷን ሁኔታ ለማጣራት ከህክምና ባለሙያዎች ጋር አየተመካከረ እንደሆነም ፖሊስ አክሎ ገልጿል፡፡

ከወ/ሮ ትዕግስት ብርሃኑ ጋር በተያያዘ ትዳራቸው የፈረሰ፣ ንብረታቸውን ያጡ ግለሰቦች እንዳሉም የፖሊስ መረጃ ይጠቁማል፡፡

አዲስ አበባ ቤቴል የተባለው ሰፈር ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ አለሚቱ በትዕግስት በደል እንደደረሰባት ቃሏን ለፖሊስ ሰጥታለች፡፡ ቤተሰቦቿ ወደ አምቦ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጉደር ከተማ የወሰዷት፣ ወ/ሮ ትዕግስት በፀበል ከህመምሽ ትፈውስሻለች በሚል እንደሆነ የተናገረችው ወ/ሮ አለሚቱ፣ ከተጠመቀች በኋላ ከቲቢ ካንሰር ተፈውሰሻል ብለው ህዝብ ተሰብስቦ በቪዲዮ እንደተቀረፀች ለፖሊስ ገልፃለች፡፡

ከዚህም በኋላ ደግሞ ልጆቼንና ወርቄን ነጥቃኛለች የምትለው ወ/ሮ አለሚቱ፣ ልጆችሽ የእኔ እንጂ የአንቺ አይደሉም መቧሏን ትናገራለች፡፡ “ አንድ ቀን የትንሿን ልጄን ፀጉር ሳበጥር ለምን ነካሻት ተብዬ እስከምዝለፈለፍ ድረስ ተደብድቤያለውሁ” ትላለች፡፡

ከእኔ የትም አታመልጡም ስለምትል ሁሉም ይፈራታል የምትለው ወ/ሮ አለሚቱ፣ ተከታዮቿ “ እመቤታችን ናት አምልኳት” እንደሚሉ ትናገራለች፡፡ “በምስል ታመልካላችሁ፤ ይሄው በአካል መጥታለች አምልኳት” ይሉናል ብላለች፡፡ በየቀኑ ፆም አለ፣ በቀን አንዴ ንፍሮ እንበላለን ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ፣ ፆሙ የአዋቂ ብቻ ሳይሆን ከስድስት ወር ጀምሮ ያለ ህፃንም እንዲፆም ይደረጋል- ለሦስት ቀን ጡት አይሰጠውም ብላለች፡፡

ወ/ሮ ትዕግስት ትምህርት ሃጢያት ነው በሚል አቋም ልጆች እንዳይማሩ እንደምታደርግም ተበዳይዋ ለፖሊስ ተናግራለች፡፡ የ12 ዓመት ልጄን ከዚህ እንግልት ለማዳን እንጥፋ ብዬው ነበር ፣ እሱ ግን ፈርቶ እምቢ አለኝ የምትለው- አለሚቱ፣ የባሰው መከራ የመጣው ግን የ3 አመት ልጄ ለ3 ቀን ያለ እህል ውሃ ፆም ፀሎት መያዝ አለበት ስትላት እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ትልቁ ልጄ አሻፈረኝ ስላለ ሌላ ሙከራ ባደርግ ይገሉኛል ብዬ ትንሿን ልጄን ይዤ ጠፋሁ ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ የወንድ ልጇ ነገር ስላላስቻላት ተመልሳ ወደ አምቦ መሄዷን ትናገራለች፡፡

ሆኖም ሰው ሁሉ ስለጠላቸው ወደ አዲስ አበባ ሄደዋል ተብላ መመለሷንና ልጇን ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማግኘቷን ገልፃ ለሳምንት ያህል አብሯት ከቆየ በኋላ እንደጠፋ ገልጻለች፡፡ ፖሊስ ልጇን ለሁለተኛ ጊዜ አግኝቶ የሰጣት ቢሆንም ተስማምተው ሊኖሩ እንዳልቻሉ እናት ትናገራለች፡፡ እኔን እንደ እናቱ ሳይሆን እንደ ጠላት ነው የሚያየኝ ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ “ ማርያምን ከሰሻት እኔ ካንቺ ጋር አልኖርም” ይላት እንደነበር ገልፃለች፡፡ ልጄ “ እኛ ምድራዊ አይደለንም፣ ሰማያዊ ነን” እያለ እሷ የምትናገረውን ሲደግም ነገሩ ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ስለገባኝ ወደ እነሱ እንዳይመለስ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተደርጓል የምትለው እናቱ አሁን ትንሽ ቢሻሻልም፣ እሷን ግን እንደጠላት እንደሚመለከታት ትናገራለች፡፡ ልጄ ጤነኛ አይደለም ያለችው ወ/ሮ አለሚቱ፣ ንብረቴን በሙሉ አጥቼአለሁ ከምንም በላይ የሚፀፅተኝ ግን ልጄን ማጣቴ ነው ብላለች- እንባዋን እያፈሰሰች፡፡

ወ/ሮ ትዕግስት አበራ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ ስትሆን ጉዳይዋ ወደ ፍርድ ቤት ተልኮ በጊዜ ቀጠሮ ላይ ነው፡፡ ወ/ሮ ትዕግስት ለፖሊስ በሰጠችው ቃል “ የሥላሴ መልዕክተኛ ነኝ፡፡ እኔ ከወንድ ጋር አልተኛሁም፤ ተርፌሳም፣ ማርያምን ዮሴፍ ይጠብቃት እንደነበር ጠባቂዬ ነው፡፡ ሦስት ልጆች ቢኖሩኝም በመንፈስ ቅዱስ ነው የወለድኳቸው፣ ይህንን ሁሉ ያደረኩት ሥላሴዎች አዘውኝ ነው፣ አላጠፋሁም” ብላለች፡፡

ምንጭ (ሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ -ሰላም ገረመው)