20120509

ለንግሥ ወደ ርእሰ አድባራት ተድባበ ማርያም ገዳም የተጓዙ 17 ሰዎች በመኪና አደጋ ሕይወታቸው አለፈ

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን አማራ ሳይንት ወረዳ በምትገኘውና ዛሬ በምትነግሠው ርእሰ አድባራት ተድባበ ማርያም ገዳም ለንግሥ በመጓዝ ላይ የነበሩ 17 ሰዎች፣ በደረሰባቸው የመኪና መገልበጥ አደጋ ከትናንትና በስቲያ ሕይወታቸው ማለፉን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ከትናንት በስቲያ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን በደረሰው የመኪና መገልበጥ አደጋ 17 ሰዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው ማለፉን፣ ሁለት ሰዎች ወደ ደሴ ሆስፒታል መላካቸውን፣ ሁለት ደግሞ ሳይንት አጅባር ህዳር 11 ሆስፒታል መግባታቸውንና አንድ ተጐጂ ደግሞ ሳይንት አጅባር ጤና ጣቢያ ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ እማኞቹ ተናግረዋል፡፡

ሕይወታቸው ካለፉት 17 ሰዎች መካከል አሥሩ እዚያው ተድባበ ማርያም ገዳም የቀብር ሥርዓታቸው በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 11 ሰዓት መፈጸሙን፣ የቀሪዎቹ አስከሬን ወደ አዲስ አበባና ወደየመጡበት አካባቢ እየተሸኘ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በ600 ኪሎ ሜትርና ከሳይንት አጅባር በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የተድባበ ማርያም ገዳም ለመድረስ ጥቂት ርቀት ሲቀር ባለው ገደላማ ቦታ ላይ ሲደርስ፣ አንድ መነኩሴና ሁለት ወጣቶች ወርደው በእግራቸው መጓዝ በመጀመራቸው ከአደጋው መትረፋቸውን እማኞቹ ገልጸዋል፡፡ በመኪና አደጋው ሕይወታቸው ላለፈውና የቀብር ሥርዓታቸው በዚያው በገዳሙ ለተፈጸመው ምዕመናን ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በተገኙበት በፈረንሳይ አቦ ቤተ ክርስቲያን ትናንት ምሽት ላይ ፀሎተ ፍትሐት መደረጉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

 ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እንመኛለን !!!!

                                                                                              ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ 

20111231

የመላእክት አማላጅነት - ክፍል ሦስት

በክፍል አንድና በክፍል ሁለት ትምህርታችን የመላእክትን አማላጅነት በተለያየ መንገድ ተመልክተናል፡፡ እነዚያን ያላነበባችሁ በፌስቡክ ኖት ውስጥ ያኖርኩአቸው በመሆኑ ያንን በመክፈት ማንበብ እንደምትችሉ ለመጠቆም እወዳለሁ!
ሦስተኛውን ክፍል እነሆ፡-

‹‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ›› ያለው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አስተምሯል፡፡ /መዝ77.2/ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የመላእክትን አማላጅነት የሚያሳይ ነው፡፡
ሙሉ የወንጌሉ ቃል ከዚህ ቀጥሎ የምናነበው ሲሆን ነጥቦቹን አንድ በአንድ እንመለከታለን፡፡

“ይህንም ምሳሌ አለ። ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም። እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት።ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው።” /ሉቃ13।6-9/

ይህን ቃል ጽፎ ያቆየልን ሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስ ቢሆንም ትምህርቱን ያስተማረው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ይህንም ምሳሌ አለ›› ብሎ ታሪኩን በመጀመሩ ትምህርቱ ምሳሌያዊ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም፡፡
የበለሲቱ ጌታ /ባለቤት/ ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ፍሬ ቢፈልግባት ምንም ስላላገኘባት እንድትቆረጥ ለሠራተኛው ጥብቅ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ሠራተኛው በፍጥነት ሊቆርጣት ይችል ነበር፡፡ ያን ቢያደርግም በጌታው ዘንድ ሊመሰገን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የታዘዘውን አድርጓልና፡፡

ነገር ግን ጌታውን ‹‹በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት›› በማለት ስለ በለሲቱ ለመነላት፡፡ አማለዳት ማለት ነው፡፡ ለሌላ ወገን የሚደረግ ልመና ምልጃ ነውና፡፡ የሚገርመው ደግሞ በለሲቱ እንዲለምንላት አልተማጸነችም፡፡ ሠራተኛው በራሱ ደግነት በፈቃዱ ተነሣስቶ ለመነላት እንጂ፡፡ ብትለምነው ደግሞ የበለጠ ሊያደርግ እንደሚችል መረዳት አያዳግትም፡፡ ሊያማልድ ያልተዘጋጀ ወይም ያላሰብ ሰው እንኳን እባክህ አማልደን ብለው ሲልኩት እምቢ እንደማይል ሁሉ ይህ ሠራተኛ ቢለመን የበለጠ ሊያደርግ መቻሉ እሙን ነው፡፡

የበለሲቱም ጌታ የቀጠርኩህ እንድትታዘዘኝ እንጂ እንድትለምነኝ አይደለም ሳይል የሠራተኛውን ምልጃ ተቀበለ፡፡ ይህም ምልጃ ተቀባይ ጌታ መሆኑን ያሳያል፡፡

ምሳሌው እንዴት እንደሚተረጎም እንመልከት፡- የበለሷ ጌታ /ባለቤት/ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ በለሲቱ ደግሞ እስራእላውያንን ቀጥሎም የሰውን ዘር በሙሉ ያመለክታል፡፡ ሠራተኛ የተባለውም ሰውን የሚጠብቅ መልአክ /ዑቃቢ መልአክ/ ነው፡፡ ከበለሲቱ በተስፋ የተጠበቀው ፍሬ ደግሞ ከሰው ዘር በሙሉ ፈጣሪ የሚፈልገው የቀና ሃይማኖትና መልካም ምግባርን ነው፡፡ ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ፍሬ ማጣቱ ፈጣሪ በታዳጊነት፣ በወጣትነትና በጎልማስነት ጊዜ ሁሉ ፍሬ እንደሚፈልግብን ያሳያል፡፡ ‹‹ቁረጣት›› ማለቱ ፍሬ ሲያጣብን ያለ ዕድሜም መቀሠፍ እንዳለና ሞት እንደሚፈረድብን ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ሠራተኛ ለበለሲቱ እንደለመነላት መላእክትም ለእኛ እንደሚለምኑልን እንደሚያማልዱን ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን መመልከት አለብን፡፡ ይህን ካልተቀበልን ምን ብለን ልንተረጉመው ነው? ‹‹ቅዱስ ጠባቂ›› የሚባል መልአክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ /ዳን4।13፤4।23/ እንዲጠብቁንም ያዘዛቸው ፈጣሪ ነው፡፡ ‹‹መላእክቱን ስለ አንተ ያዛቸዋል፡፡›› ተብሏልና፡፡ /መዝ90।11/

ይህ ምሳሌያዊ ትምህርት በርካታ መልእክቶችን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ቃልና ዐረፍተ ነገርም ብዙ ምሥጢር ይዟል፡፡ የእኛ ርእስ ግን ስለ ምልጃ ስለሆነ በዚህ እንወሰናለን፡፡ ይሁን እንጂ ጎላ ያለ ጥያቄ መልሶ ለማለፍ ያህል አንድ ሰው የበለሲቱ ባለቤት ‹‹ትቆረጥ›› ሲል ሠራተኛው ደግሞ ‹‹በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት›› ማለቱ ለበለሲቱ ከባለቤቱ ይልቅ ሠራተኛው ያዘነላት አያስመስልም? ሊል ይችላል፡፡
ለበለሲቱ ከሠራተኛው ይልቅ ያዘነላት ጌታዋ ነው እንጂ ሠራተኛው አይደለም፡፡ እንዴት ቢባል ጌታዋ ከአንድም ሦስት ጊዜ ሳይቆርጣት አልፎአታል፡፡ በተጨማሪም ሠራተኛው የለመነላት ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እንዲያው ከዚያ በኋላ ካላፈራች ‹‹ትቆርጣታለህ›› ሲል ተናገረ፡፡ ጌታዋ ለሦስት ጊዜ የታገሣትን እርሱ ግን አንዴ ከለመነላት በኋላ ብትቆረጥም ቅር እንደማይለው አስረዳ፡፡ ታዲያ ከጌታዋ ይልቅ እርሱ ራራ ለማለት እንዴት ይቻላል? በዚያውም ላይ ያ ሠራተኛ ቢለምንላትም ይቅር ያላት ግን ጌታዋ መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር እንዲህ አዝኖ የሚያማልዳትን ሠራተኛ ያዘዘላት እኮ ጌታዋ ነው፡፡ በመጨረሻ ትምህርቱ ምሳሌያዊ ነው፡፡ ‹‹ቁረጣት›› ያለው ጌታዋ የፈጣሪ ምሳሌ እንደመሆኑ መጠን ሠራተኛው የሚያቀርብለትን የምልጃ ጥያቄ አስቀድሞ ያውቃልና በለሲቱ እንደማትቆረጥ ያውቅ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እርሱ በበለሲቷ ላይ ያለውን የማዘዝ ሙሉ ሥልጣን እና የሠራተኛውን ማለትም የጠባቂ መልአኩን የማማለድ ሥራ ሊያሳይ በሚችል መንገድ ምሳሌውን እርሱ ባወቀ መስሎ ተናገረ፡፡

-በቃል የሚጠና ጥቅስ ሉቃ 13।6-9
-ሐሳብ - የበለሲቷ ምሳሌ
-ትምህርት - በሠራተኛው ልመና አንጻር የመላእክትን አማላጅነት ማሳየት

ይቆየን!

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነትና ተራዳኢነት የፈጣሪ ቸርነት አይለየን!



20111230

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ክፍል 2

በክፍል አንድ ትምህርታችን መቆም የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ፍቺ ይዞ የሚገኝበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አይተን ነበር፡፡ አያይዘንም የመላእክትን አማላጅነት ከዚሁ ቃል አንጻር ተረድተናል፡፡ በክፍል ሁለት ትምህርታችን ደግሞ ማየት ከሚለው ቃል አንጻር የመላእክትን አማላጅነት እንማራለን፡፡

መቆም እንደሚለው ቃል ሁሉ ‹‹ማየት›› የሚለው ቃልም በመጽሐፍ ቅዱስ የራሱ የሆነ አገባባዊ ፍቺ አለው፡፡ በዓይን መለማመጥ፣ ማሳዘን፣ መቆጣት፣ ተስፋ ማድረግ እና ማስፈራራት ይቻላል፡፡ ‹‹የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፡፡›› እንዲል፡፡ (መዝ 144.15) ስለዚህ ‹‹ማየት›› መመርመር ወይም ንስሐ መግባት፣ መለመን፣ መጸለይ፣ ተስፋ ማድረግ፣ ማማለድ፣ መስማት፣ መቀበል፣ መቆጣት ወዘተ የሚሉ ፍቺዎች አሉት፡፡

ማየት የሚለው ቃል ከ እግዚአብሔር አንጻር

በተለይ ከእግዚአብሔር አንጻር ካየነው ማየት የሚለው ቃል መስማት፣ መቀበል፣ ይቅር ማለት የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ "እግዚአብሔር እገሌን በዓይነ ምሕረት አየው" ማለት አሰበው፣ ጎበኘው፣ ማረው፣ ሰማው ፣ ይቅር አለው ማለት ይሆናል፡፡ እንደ አገባቡ ተቆጣው ማለትም ሊሆን ይችላል፡፡ ለጠቀስናቸው ሐሳቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፡፡››፤ ‹‹እነሆ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፡፡››፤ ‹‹የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮውም ወደ ጩኸታቸው ነው፡፡›› የሚሉትን ማስረጃዎች መመልከት ብቻ እንኳን ይበቃል፡፡ (ዘፍ 4।4፤ መዝ 32।18፤ 33।15)

ከፍጥረት አንጻር

"ማየት" የሚለውን ቃል ከሰው አንጻር ወይም ከፍጥረት ሁሉ አንጻር ካየነው ደግሞ ሌሎች ፍቺዎች ይኖሩታል፡፡ ‹‹አቤቱ አምላኬ እየኝ ስማኝም፡፡›› ሲል ማረኝ ለማለት ነው፡፡ "ማየት" መመርመር ሲሆን ‹‹ራስህን ለካህን አሳይ›› ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ራስህን አስመርምር፣ ንስሐ ግባ ማለት ነው፡፡ (ማቴ8.4፤ መዝ12.3) በእንግሊዝኛውም ይህን የመሰለ ነገር አለ፡፡ ነጮቹ ሕክምና ላድርግ ወይም ልመርመር ለማለት ‹‹ሐኪሜን ልይ›› ይላሉ፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ‹‹ማየት›› የሚለውን ቃል ትርጉም በትክክል በመረዳት የመላእክትን አማላጅነት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ለሰው ልጆች በሙሉ ለየራሳቸው ጠባቂ መላእክት አሏቸው፡፡ ይህንንም ያደረገው ፈጣሪ ነው፡፡ ‹‹መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና›› የሚለው የነቢዩ የዳዊት መዝሙር ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሚጠብቋቸው መላእክትን እንዳዘጋጀ ያስረዳል፡፡ (መዝ90.11) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌያዊ ትምህርቱ ለበለሱ አትክልተኛ መቅጠሩ በበለስ ለተመሰሉ የሰው ልጆች ለእያንዳንዳቸው ጠባቂና ተንከባካቢ መልአክ ማዘጋጀቱን የሚያስረዳ ነው፡፡ (ሉቃ13.6-9) በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ መልአኩ ‹‹ቅዱስ ጠባቂ›› የተባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ (ዳን4.13፤ 4.23) በተጨማሪም ለሰው ልጆች ሁሉ ጠባቂ መልአክ እንዳላቸው በወንጌል ‹‹መላእክቶቻቸው›› በሚል የተቀመጠው ቃል ብቻ ምስክር ነው፡፡ (ማቴ18.10)

መላእክት እንደ ታላላቅ ወንድሞቻችን የምንቆጥራቸው እነርሱም ደግሞ እኛን እንደ ታናናሽ ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው የሚያዩን ቤተሰቦቻችን ናቸው፡፡ እነርሱ ከእኛ በፊት በዕለተ እሑድ የተፈጠሩ የአምላክ ልጆች ሲሆኑ እኛ ደግሞ በዕለተ ዐርብ የተፈጠርን የእግዚአብሐር ልጆች ነንና፡፡ (ኢዮ1.6፤ 2.1፤ ዮሐ1.12) የአንድ አባት ልጆች ደግሞ ወንድሜ እኅቴ እንደሚባባሉ የታመነ ነው፡፡ ስለዚህ መላእክት እየሳሱ ይጠብቁናልና እኛ የእነርሱ ገንዘብ ነን፡፡ እነርሱም የእኛ ገንዘቦች በመሆናቸው ‹‹መላእክቶቻቸው›› ተብለዋል፡፡ ይህም ከወንጌሉ ትረካ የምናታገነው ነው እንጂ በብልሃት የተፈጠረ ቃል አይደለም፡፡

እነዚህ ጠባቂ መላእክት ስለ ሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያዩ ወንጌል ይናገራል፡፡ ‹‹መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉና›› እንዲል፡፡ (ማቴ18.10) ይህም ዐረፍተ ነገር ያለ ምንም ጥርጥር የመላእክትን አማላጅነት የሚያሳይ ነው፡፡ ማየት መጸለይ ማማለድ የሚል ትርጉም እንዳለው ቀደም ሲል በሚገባ ተቀምጧልና፡፡ ካልሆነ ግን በምን ሊተረጎም ይችላል? የጥቅሱን ሙሉ ሐሳብ ስንወስድ ሰዎችን አትናቁ! የምትንቋቸውን ሰዎች የሚጠብቁ መላእክት ዘወትር የአባቴን ፊት ያያሉ የሚል ነው፡፡ ይህም ለተናቁት ሰዎች ለምነው ያማልዷቸዋል፡፡ የምትንቁትን እናንተን ደግሞ ጸልየው ያስፈርዱባችኋል የሚል ማስጠንቀቀቂያ ቃል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ለማጠቃለል በቃል የሚጠና ሐሳብና ጥቅስ

ጽንሰ ሐሳብ፡- "ማየት" መጸለይ፣ ማማለድ፣ መስማት፣ መቀበል፣ ይቅርታ ማድረግ ማለት ይሆናል፡፡ እንዲህ ከሆነ መላእክት ስለ እኛ የፈጣሪን ፊት ያያሉ ማለት ያማልዳሉ ማለት ነው፡፡

በቃል የሚጠኑ ጥቅሶች

1ኛ. "ማየት" መስማት፣ መቀበል ሲሆን በፈጣሪ አንጻር

(ዘፍ4.4፤ መዝ32.18፤ 33.15)

2ኛ."ማየት" መጸለይ፣ ማማለድና ይቅርታ መጠየቅ ሲሆን ከፍጡር አንጻር

(ማቴ18.10፤ ማቴ8.4፤ መዝ12.3)

ይቀጥላል

የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት - ክፍል አንድ

ቅዱሳን መላእክት አማላጆቻችን ናቸው፡፡ ስለ ቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ተጽፏል፡፡ ይህንንም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጥቀስና ትክክለኛ ትርጉማቸውን በምንረዳበት ጊዜ የምናገኘው ነው፡፡
ሐሳቡን በትክክል ለመያዝና ለማጥናት እንዲረዳን የመላእክትን አማላጅነት በስድስት ዋና ዋና መንገዶች ከፍለን ለማየት እንችላለን፡፡
ለዛሬ ከስድስቱ የመጀመሪያውን እነሆ፡-
1ኛ. መቆም የሚለውን ቃል ትክክለኛ ትርጉም በመረዳት፡- መቆም የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ እንደየአገባቡም ትርጉሙ የተለያየ ነው፡፡ መቆም የሚለው ቃል ከያዛቸው ትርጓሜዎች አንዱ ማማለድ የሚል ነው፡፡ መቆም ከተኙበት ወይም ከተቀመጡበት መነሣት፣ በእግር ቀጥ ማለት፣ መጽናት፣ በክብር መቀመጥ ወዘተ የሚሉ ሌሎች ትርጓሜያትም አሉት፡፡ ስለዚህ እንደየአገባቡ ታይቶ ይፈታል እንጂ ሁል ጊዜ ቃሉን በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ መመልከት ከስሕተት ላይ ይጥላል፡፡
ለዚህ ሁሉ አገባብ ማስረጃ ብትሻ እነዚህንና ሌሎችንም ጥቅሶች በሚገባ ፈትሽ፡፡ ‹‹የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ›।፣ ‹‹የደመናው ዓምድ ቆመ››፣ ‹‹በሃይማኖት ቁሙ›› (ሉቃ8।44፤ ዘዳ31.15፤ ዘኁ10.12፤ 1ቆሮ16.13) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ መቆም የሚለው ቃል የተለያየ ሐሳብ ይዞ መገኘቱን ልብ ማለት ያሻል፡፡

አሁን ከዚህ ቦታ ከርእሳችን አንጻር እኛ የምንፈልገው ቆመ የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም ይዞ መገኘቱን መረዳት ነው፡፡ መቆም ሲባል ማማለድ የሚል ትርጓሜ እንዳለው ለመረዳት ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተጻፈውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እስራኤላውያን ጣዖት በማምላክ ፈጣሪቸውን አስቆጡት፡፡ እርሱም ሊያጠፋቸው ጀመረ፡፡ ነገር ግን ሙሴ እነዚህን ሕዝቦች ከምታጠፋ እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስኝ በማለት በራሱ ፈርዶ አማለዳቸው፡፡ ፈጣሪም የሙሴን ልመና ሰምቶ መዓቱን በትዕግሥት መለሰ፡፡ ይህ ታሪክ በዘፀአት የኦሪት ክፍል ተመዝግቧል፡፡ (ዘፀ32।32)
ይህንን የሙሴ ምልጃ ቅዱስ ዳዊት በሌላ ጊዜ በድጋሚ ተርኮታል፡፡ ይኸውም በዳዊት መዝሙር የምናገኘው ነው፡፡ ነገር ግን አተራረኩ መቆም ማማለድ መሆኑን በግልጽ በሚያሳይ መንገድ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያዳናቸውን እግዚአብሔርን ረሱ፡፡ እንዳያጠፋቸው ቁጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ፡፡›› የተሰመረበትንና ደምቆ የተጻፈውን ኃይለ ቃል ልብ ብለህ ተመልከት፡፡ (መዝ015।23) ባይቆም ኖሮ ሲል ባያማልዳቸው፣ ባይለምንላቸው፣ ባይጸልይላቸው ኖሮ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ መቆም የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም እንደሚኖረው እንረዳለን፡፡
ዳግመኛም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች (መላእክት) በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፡፡ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ›› ይለናል፡፡ ‹‹ለመቆም›› ሲል ለመለመን፣ ለማማለድ ማለት ነው፡፡ አብሮአቸውም ሰይጣን መምጣቱን ልብ በል፡፡ ሰይጣን የመጣው ለምን ነበር? ጻድቁ ኢዮብን ለመፈተን ፈቃድ ያገኝ ዘንድ ፈጣሪውን ለመለመን አልነበረምን? የመላእክትም አመጣጥ ፈጣሪቸውን ስለሰው ለመለመን እንጂ ለሌላ አልነበረም፡፡ ይህን ሲገልጥ ‹‹ለመቆም መጡ›› ይለናል፡፡ መቆም መለመን፣ ማማለድ ማለት ነውና፡፡ (ኢዮ1।6) መቆም ማለት መጸለይ፣ ማማለድ የሚል ፍቺ እንዳለው ካስጨበጡ በኋላ ይህንን ቃል በመጠቀም የመላእክትን አማላጅነት ማስረዳት ቀላል ይሆናል፡፡

ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኛ ከምናውቀው ውጭ አንዳንድ ጊዜ በተቃራኒ አቅጣጫም እንኳን ፍቺ ይዘው ይገኛሉ፡፡ አገባባቸውን እንደመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤና ምሥጢር መማር የሚያስፈልገው ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ለብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጡ ቃላትን ትክክለኛ መንፈስ አለመረዳት የመላእክትን አማላጅነት እንዳይረዱ አድርጓቸዋልና፡፡
ለምሳሌ፡- ቅዱስ ገብርኤል ራሱ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው መልአኩ ገብርኤል ነኝ፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ ይህም በቅዱስ ወንጌል የተጻፈ ኃይለ ቃል ሲሆን አብዛኞቻንን እናውቀዋለን፡፡ ልዩ የሚሆነው ግን የቃሉን ትክክለኛ አገባባዊ ትርጉም ባለማወቃችን ምክንያት መልአኩ ይህን ባለ ጊዜ ‹‹እኔ አማላጅ ነኝ›› እንዳለን አድርገን አለመረዳታችን ነው፡፡ መቆም ማለት ማማለድ የሚል ትርጉም ካለው ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የምቆም›› ማለት ደግሞ ‹‹የማማልድ›› ማለት መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅነቱን ራሱ ግልጽ በሆነ መንገድ ነግሮናል ማለት ነው፡፡
እስኪ እናንተ ፍረዱ! በዚህ ስፍራ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅ ነኝ ማለቱን ካላመንን ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው›› ማለቱን ምን ብለን እንረዳዋለን? የእግዚአብሔር ፊቱ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ነው እንጂ እንደፍጡር ወደ አንድ ገጽ የተወሰነ አይደለም፡፡ መላእክት ደግሞ በተፍጥሯቸው እንደ ሰው ልጅ የሚታጠፍና የሚዘረጋ እግረ ሥጋ ስለሌላቸው አይቀመጡም፤ አይተኙምም፡፡ ታዲያ አማላጃችሁ ነኝ ማለቱ ካልሆነ በቀር መልአኩ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው›› ሲል ምን ማለቱ ነው? መልአኩ እግዚአብሔርን እንደ ምድራዊ ንጉሥ ራሱን ደግሞ እንደ ንጉሥ ወታደር ቆጥሮ በንጉሡ ፊት ቀጥ ብዬ የምውል ዘበኛ ነኝ ማለቱ ነውን? በፍጹም አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር ቤት ደጅ አፍ መቆምና በእግዚአብሔር ፊት መቆም ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ምሥጢራቸውም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ (ራእ21।12፤ ዘፍ3.24) ይልቅ ሊሆን የሚችለው እኔ በፊቱ ባለሟልነት ያለኝ ሁሉ ጊዜ ስለ እናንተ የማማልድ ነኝ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
መልአኩ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ለምንድን ነው? ለማመስገን ነው እንዳንል ይህንን ሐሳብ ለካህኑ ለዘካርያስ መንገር ለምን አስፈለገው? የሚል ጥያቄ ያስነሣል፡፡ ትርጉሙ እንዲህ ቢሆን ወደ ካህኑ ወደ ዘካርያስ ከመጣበት ጉዳይ ጋር ንግግሩ ምንም ግንኙነት አይኖረውምና ይህን መናገር አያስፈልገውም፡፡ ከዚህ ይልቅ እኔ ሰዎችን ሁሉ ለማማለድ በእግዚአብሔር የምቆም ባለሟልነት ያለኝ መልአክ በመሆኔ የለመንከው ልመና መድረሱን የምሥራች ልነግርህ ብመጣ ቃሌን እንዴት ትጠራጠራለህ? ለማለት ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው መልአኩ ገብርኤል ነኝ›› በማለት መልአኩ ይህን ተናገረ ብንል ከሁሉ በላይ የሚያስኬድና ለአእምሮ የሚመች ትክክለኛ ትርጓሜ ነው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ስለ ቅዱስ ሚካኤልም በትንቢተ ዳንኤል ላይ እንዲህ ተጽፏል፡፡ ‹‹በዚያ ወራት ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል›› ይላል፡፡ (ዳን12.1) በዚህ ጥቅስ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው›› ተብሏል፡፡ እረ ለመሆኑ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ‹‹የሚቆመው›› ለምንድር ነው? ለማማለድ አይደለምን? ይህን ካልተቀበልን ቃሉን ምን ብለን እንተረጉመዋለን? ለማመስገን ይቆማል እንዳንል ቃሉ የሚለው ‹‹ስለ ሕዝብ ልጆች የሚቆመው›› ነው፡፡ ስለ እኛ ጥብቅና ይቆማል እንዳንል ወደ ባሰ ስሕተት ይወስደናል፡፡ ሚካኤል በእግዚአብሔር ፊት ጥብቅና አይቆምምና፡፡ እግዚአብሔርም በጠበቃ የሚሟገቱት አምላክ አይደለምና፡፡ ጥብቅና ይቆማል ከማለት ይልቅ ትክክለኛውና የሚስማማው ወደ ፈጣሪ ሊለምንልን ወይም እኛን ለማማለድ ይቆማል የሚለው ትርጓሜ ነው፡፡ አስቀድሞ እንደተመለከትነው ‹‹መቆም›› የሚለው ቃል ማማለድ የሚል ትርጉም አለውና፡፡
ይህ ለምሳሌ ያህል ተጠቀሰ እንጂ በፈጣሪ ፊት እልፍ አእላፋት መላእክት ለምልጃ ይቆማሉ፡፡ ቅዱስ ዳንኤል ‹‹ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፡፡ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፡፡›› በማለት የገለጸው ይህንን እውነት ነው፡፡ (ዳን7.9-11)
ከዚህ በላይ ከብሉይ ስለ ቅዱስ ሚካኤል ከሐዲስ ደግሞ ስለ ቅዱስ ገብርኤል የተጻፉት ለማስረጃነት ተጠቅሰዋል፡፡ የተማሩትንና ያነበቡትን በልብ ለመክተብ መላልሶ ማንበብና ማጥናት እንደሚያስፈልግ እሙን ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ብትሻ የቅዱስ ገብርኤል ዝክረ በዓል ወር በገባ በአሥራ ዘጠኝ እንደሚውል ታውቃለህ፡፡ ስለ እርሱም የተጠቀሰው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1.19 መሆኑን ልብ በልና ጥቅሱ ከወርኃዊ በዓሉ ጋር ያለውን ዝምድና መርምር፡፡ ማለትም ቁጥር 19 ላይ መጻፉን አስተውል፡፡ ስለ ቅዱስ ሚካኤልም እንዲሁ አድርግ፡፡ ጥቅሱ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 12 ላይ ይገኛል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ወርአዊ ክብረ በዓሉም በ12ኛው ቀን ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ይህንንና ይህን የመሰለ የራስህን የማጥኛ ዘዴ በመጠቀም ጥቅሶቹን በቃልህ ለማጥናት ሞክር፡፡
ለማጠቃለል በቃል የሚጠና ሐሳብና ጥቅስ

ጽንሰ ሐሳብ፡- መቆም ማማለድ ማለት ይሆናል፡፡ የዚህ ማስረጃው (መዝ105.23፤ ኢዮ1.6) ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ መላእክት ስለ እኛ በፈጣሪ ፊት ይቆማሉ ማለት ያማልዳሉ ማለት ነው፡፡
በቃል የሚጠኑ ጥቅሶች
1ኛ।ሉቃ1:19
2ኛ।ዳን12:1
3ኛ।ዳን7:9-11

እነዚህን ማጥናት አያቅትምና አጥንቶ ለልጆች በማስጠናት የወላጅነት ግዴታችንን በዚህ መንገድ እንወጣ!
ይቆየን!
ከዲያቆን ኅብረት የሺጥላ