20111225

ቅድስት ማርያም ግብጻዊት



የኢየሩሳሌም ሊቀፓፓስ ሳፍሮኒዮስ እንደጻፈው:- ቅድስት ማርያም ግብጻዊት የተወለደችው በግብጽ ነዉ::ከዚያም የዝሙት ፍቅር አድርባት:ለ17 አመት ያህል ሰዎችን በሚያቃጥል የኃጥያት እሳት ታስፈጃቸው ነበር ዝሙት እየሰራች:ብዙዎችንም ታስት ነበር:: ዝሙት ከመውደዷ የተነሳ ገንዝብ እንኳን ልስጥሽ ሲሉ አትቀበልም ነበር:: በእግዚአብሔርም አታምንም ነበር በዛው ፋንታ እንደፈለገች ትሆን ነበር:: በልቧ ከዚህ ስራዬ ማንም አይከለክለኝም ትል ነበር:: አንድ ቀን ሊቢያውያን እና ግብጻውያን ወደ ባህር እየተቻኮሉ ሲሄዱ አይታ ወዴት እንደሚሄዱ ብጠይቃቸው የከበረ የጌታችንን መስቀል በዓል ለማክበር ወደ እየሩሳሌም እንደሚሄዱ ሲነግሯት እና የሚሄደው ሰው ብዙ መሆኑን ስታይ: ብዙ ዘመዶችን አገኛለው ብላ ከእነርሱ ጋር ለመሄድ ተነሳች:ለጉዞዋ ወይም ለምግብ የሚሆን አንድም ገንዘብ አልያዘችም ነበር:: በኃላም በሰውነቷ ማማር ብዙዎችን በዝሙት ምክንያት አጠመደች ወደ ተቀደሰ ቦታ የሚሄዱቱን ሰዎች በማሳት ዋና የሰይጣን መረብ ሆና ነበር:: በዚህም ስራዋ እየተኩራራች ለሰው ሁሉ ትናገር ነበር:የሐጥያተኛን ሞት የማይወድ እግዚአብሔር መመለሷን እየጠበቀ ይታገሳት ነበር:: በመጨረሻም እየሩሳሌም ደርሰው ከበዓሉ በፊት እንደለመደችው እንደውም በከፋ መልኩ ዝሙትን አብዝታ ትሰራ እና ሰውንም ታስት ነበር:: የበዓሉ ዕለት ጠዋት ብዙ ተሳላሚዎች ጌታችን መቃብር ላይ ወደ ተሰራችው ቤተ-ክርስቲያን ሊሳለሙ ሲሄዱ አየችና እዛ ሄደው ምን እንደሚያደርጉ ለማወቅ ፍላጎት አደረባት እናም ህዝቡ በሚገቡበት በር እየተጋፋች ለመግባት ትሞክር ጀመር በኃላም በሩ ጋር ስትደርስ የሆነ ሐይል ሲገፋት ይታወቃት ጀመር ሌሎቹን ሰዎች ስታይ በቀላሉ ሲገቡ ታያለች መጀመሪያ ላይ ምንድን ነው እያለች ትስቅ ነበር ደጋግማ ስትሞክር አልቻለችም በኃላም ዝም ብላ በሩ ላይ ቆመች እንደገናም ደጋግማ ሞከረች ልትገባ ግን አልቻለችም !! ሲደክማት ብላ ከበሩ አጠገብ ቆመች በህሊናዋም በብዙ መከራ ምን እንደሆነ ታስብ ጀመር:: ቅዱስ መስቀሉን ለማየት እርሷ ያልቻለችበትን ምክንያት ታስብ ጀመር:የድህነት ቃል የልቦናዋን አይኖች ነካቸው እንዳልገባ የከለከለኝ የራሴ ሃጥያት ስትል አሰበች (ተረዳች):: በኃላም በማልቀስ እና ደረቷን እየደቃች ከውስጣዊ ልቧማዘን ጀመረች:: "ለምን አልገባም? እንዳልገባ የከለከለኝ የኃጢአቴ ብዛት ነውን?" እያለች ደጋግማ እራሷን ትጠይቅ ጀመር:: ያን ግዜ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማሪያምን ስዕል ከበሩ ላይ አየችና ሄዳ ስዕሉ ፊት ቆማ የስዕሉን ግርማና ውበት ባየች ግዜ ያለፈ የእራሷ ሃጥያት ወለል ብሎ ታያት እና አፈረች::ከዚህም በኃላ በብዙ ለቅሶ ከ ቅድስት ድንግል ማሪያም ስዕል ስር ወድቃ "ከእንግዲህ በኃላ ለጌታየ አገልጋይ ለአንቺም ባርያ እሆን ዘንድ እድል አገኝ ይሆን ?" እያለች ታለቅስ እና ትለምን ጀመር:ጌታችንንም ካለችበት ስቃይና መከራ እንዲያድናት እና በመንገዱ እንዲመራት ለመነችው:"ቅዱስ መስቀሉን ካየው በኃላ አለም እና ደስታዋን እንደምክድ ቃል ገባለው" ብላ ቃል ገባች:: ከጸለየችም በኃላ የመተማመን ስሜት ተሰማትና ወደ መስቀሉ ቦታ ወደሚያስገባው ቦታ ሄደች ከዚያም ያለችግር ገባች በኃላም መስቀሉ ጋር ደርሳ በመንቀጥቅጥ እና በብዙ እምባ ሳመች የእግዚአብሔርን ሚስጥር እና ንስሃን እንዴት እንደሚቀበል አየች:: ከዚያም ወጣ ቃል ወደ ገባችበት ወደ እመቤታችን ስዕል ጋር ሄዳ "የኃጥአንን ንሰሐ ባንቺ አማላጅነት የሚቀበል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!! አሁን የገባውትን ቃል እፈጽም ዘንድ ግዜው ነው እጄን ይዘሽ ወደ ንስሃ ምሪኝ" አለች:: ያን ግዜ የእመቤታችን ስዕል አፍ አውጥታ "ዮርዳኖስን ብትሻገሪ እረፍት ታገኛለሽ" አለቻት:ከዛም እመቤቴ ሆይ አትተዪኝ ብላ አለቀሰች እና ከዚያ ተነስታ ወደ በረሃው ጉዞ ጀመረች ከመንገዶኞቹም አንዱ እህቴ ሆይ እንኪ ብሎ 3 ሳንቲም ሰጣት እና በእነርሱ ለመንገዷ የሚሆን ዳቦ ገዝታ እያለቀሰች ከከተማው ወጣች:መንገድ ላይም መሸባትና የዮሃነስ መጥምቅ ቤት-ክርስቲያን አግኝታ እዛው ስታለቅስ አደረች:: ጠዋትም አስቀድሳ እመቤታችንንም አንቺ ተከተይኝ እያለች ጉዞዋን ጀመረች ጀልባም ፈልጋ ዮርዳኖስን ተሻገረች ከዚያም ወደ አንድ በረሃ ደረሰች:: በዚያም እህልም ሰውም ሳታገኝ ለ47 አመታት እየተጋደለች ወደሱ የሚመለሱትን ከሚቀበል ፈጣሪ ጋር ኖረች::


ከ47 አመትም ከዚህ በኋላ ዞሲማስ የተባለ መነኮስ እመቤታችን አነሳስታ ልካው ቢሄድ ከሩቅ አያት :: ዕርቃኗን ነበረችና ተነስታ ሮጠች :: (እጅግ ከመክሳቷ የተነሳም ሰው መሆኗ አያስታውቅምም ነበር ):: ዞሲማስም ያየሁት ምንድነው ? በረከት ቀረብኝ ብሎ ተከትሏት ሮጠ :: ጥቂት ተሯሩጠውም ወደ ጉድጓድም ገባች :: መለስ ብላም "ከእኔ ጋር ልትነጋገር ከወደድክ እርቃኔን ነኝና ጨርቅ ጣልልኝ " አለችው :: እርሱም መደረቢያውን ጣለላት :: ያንን ለብሳ ወጥታ እጅ ተነሳሱ :: ስላሳለፈችው እና ስለነበራት ህይወት አጫወተችው:ከዛም ለመጀመሪያው 17 አመታት የነበረባትን ፈተና እንዲ አለችው ""አባት ዞሲማስ ሆይ 17 አመት በዚ በረሃ ከአራዊት ከክፉ ምኞት እና ከክፉ ህሊና ጋር ስታገል ኖርኩ:ያለፈ ህይወቴንና ያሳለፍኩትን ደስታ እያሰብኩ እፈተን ነበር:ከረሃብ እና ከውሃ ጥም እንዲሁም ከጸሃይ ሃሩር የተነሳ በጣም ተሰቃይቻለው: ብዙ ግዜ እታመምና ለሞት እደርስም ነበር: ጌታዬም እንዲረዳኝ እለምነው ነበር ህሊናየን መጀመሪያ ወደ ተቀበለችኝ እመቤቴም ስዕል እሄድና እማጸናት ነበር ከዛም በኃላ በ4ቱ ማእዘን የሚያበራ ብርሃን አይ ነበር""እያለችና ሌላም ሌላም ትነግረው ነበር:ከዛም ቅድስት ማሪያም ግብጻዊት በብዙ ተጋድሎ ሰይጣንን ድል ነስታ ቅዱስ ዞሲማሲን በሚቀጥለው አመት ወደዚ በረሃ ስትመጣ የጌታችንን ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን በዕለተ "ፀሎተ-ሃሙስ" ይዘህልኝ በዮርዳኖስ ባህር ዳር እንገናኝ አለችው ና ተመልሳ ወደ በረሃው ገባች በአመቱን ቅዱስ ዞሲማስ ይዞላት መቶ የዮርዳኖስ ባህርን እየተራመደች ስትመጣ ግዜ አይቶ እግዚአብሄርን እያመሰገነ ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን አቀበላት ከዚያም እንደገና ቅዱስ ዞሲማስን አሰናበተችውና በሚቀጥለው አመት እንዲመጣ ነገረችው በኃላም በዓመቱ ሲመጣ አጣት እና እጂግ አለቀሰ ከዚያም ፈልጎ እሬሳዋን አገኘውና ስሟን ባለማወቁ ሲጸጸት ጊዜ አንድ ብጣቂ ወረቀት አገኘና አነበባት "" አባት ዞሲማስ ሆይ በጸሎተ ሃሙስ ማታ ከቅዱስ ሚስጥር ከተቀበልኩ በኃላ ወደ አምላኬ ሄጃለው የደካማይቱን የማርያምን ስጋ በዚህ ቦታ ቅበረው ዓፈር ወደ ዓፈር ይመለስ ዘንድግድ ነው እና ስለ እኔም ጸልይልኝ ስሟን በማወቁ ደስ እያለው እዛው ቀበራት እና ወደ ቤቱ ተመለሰ:: ቅድስት ማርያም ግብጻዊት ያረፈችው በሚያዚያ 6,522ዓ.ም. ነው:: በረከቷ ረድኤቷ በሁላችን ላይ ይደር !! አሜን !!!!

20111222

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል


የሰው ልጅ በገነት እንደ ቅዱሳን መላእክት በቅድስና አምላኩን በማመስገን በደስታ ይኖር ነበር ፡፡ ነገር ግን “ክፉና ደጉን ከምታሳውቀው ዕፀ በለስ እንዳትበላ” ተብሎ የተሰጠውን ትእዛዝ በመተላለፉ ምክንያት ከአምላኩ ተለየ(ዘፍ.3፡6) ፡፡እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው ክብሩን አጣ፣ ጸጋው ተገፈፈ ፣ ፈጣሪውንም አሳዘነ ፡፡ ቅዱሳን መላእክትም በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረው ሰው ከክብሩ ተዋርዶ ሲመለከቱ ተከዙ ፡፡
የሰው ልጅ ጠፍቶ እንዲቀር ያልወደደው እግዚአብሔር ወልድ ሰውን ለማዳን ራሱን ዝቅ አድርጎ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ ነስቶ ተወለደ ፡፡ቅዱሳን መላእክትም ከላይ ከአርያም ከአባቱ ሳይለይ እግዚአብሔር ወልድ ሰውን ለማዳን ሲል በግዕዘ ሕፃናት ተወልዶ ፣በእናቱም እቅፍ ሆኖ ፤ እንስሳት እስትንፋሳቸውን እያሟሟቁትበማየታቸው ተደነቁ ፡፡ሰውን ለማዳን ሲል ራሱን ዝቅ በማድረግ የባርያውን አርአያ እንደነሣ አስተውለው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት፣ ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ”(ሉቃ.2፡14) ብለው አመሰገኑት ፡፡
ጌታችንም በመስቀሉ የማዳን ሥራውን ሲፈጽም ተጎሳቁሎ የነበረውን የሰው ባሕርይ ወደ ቀድሞ ክብሩ መለሰው፡፡ ስለዚህም እንደ ቅዱሳን መላእክት አምላኩን ለማመስገን እድሉን አገኘ ፡፡ (ዮሐ.4፡23) ነገር ግን ከእነርሱ ጋር በመሆን ሙሉ ለሙሉ በምስጋና የሚሳተፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሙታንስ በሚነሡበት ጊዜ በሰማያት እንደ እግዚአብሔር መልአክት ሆነው ይኖራሉ…….”(ማቴ.22፡30)እንዳለው በትንሣኤ ዘጉባኤ ነው ፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን በዚህ ምድር ሳለን ከእኛ የሚጠበቅብንን ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ያስተማረንን፣ በሥራም ያሳየንን ተግባር ተግብረን፣ እንደ ቅዱሳን መላእክት ለአምላካችን በመንፈስና በእውነት በመሆን አምልኮታችንን እንድንፈጽም የእነርሱ ተራዳኢነት በእጅጉ ያስፈልገናል ፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “መላእክት ሁሉ መናፍስት አይደሉም? የዘለዓለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ ስለ አላቸው ሰዎችስ ለአገልግሎት ይላኩ የለምን?”(ዕብ.1፡14) ማለቱ ፡፡ “የዘለዓለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ” የተባልነው ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ “እነርሱ በእውነት ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ስለእነርሱ ራሴን እቀድሳለሁ፡፡ የምለምንህም ስለ እነዚህ ብቻ አይደለም፤ በቃላቸው ስለሚያምኑብኝ ሁሉ ነው እንጂ”(ዮሐ.17፡19-20)እንዳለው በክርስቶስ አምነን ለተጠመቅነው ክርስቲያኖች ነው፡፡

እናት ልጁዋን እንድትንከባከብና እንድታገለግል ሁሉ ቅዱሳን መላእክትም የዘለዓለም ሕይወትን እንድንወርስ ይራዱናል፡፡ (ሉቃ.13፡6-9) ያለ እነርሱ እርዳታና ድጋፍ በቅድስና ሕይወት አድገን የመንግሥቱ ወራሾች መሆን አይቻለንም ፡፡ እንዲህም በመሆኑ በመንፈስ ቅዱስ የልጅነት ጸጋን ከማግኘታችን በተጨማሪ ቅዱሳን መላእክት እኛን ይራዱን ዘንድ ጠባቂ ተደርገው ተሰጥተውናል ፡፡ (ማቴ.18፡10)

ቅዱስ ጳውሎስ “እናንተ ግን የሕያው እግዚአብሔር ከተማ ወደምትሆን ወደ ጽዮን ተራራ በሰማያት ወደ አለችው ኢየሩሳሌም ደስ ብሎአቸው ወደሚኖሩ አእላፍ መላእክትም ደርሳችኋል”(ዕብ.12፡22) በማለት እንደተናገረው በክርስቶስ የማዳን ሥራ ከቅዱሳን መላእክት ጋር አንድ ቤተሰብ መሆንን አግኝተናል ፡፡ ስለዚህም ጉዞአችንን ጨርሰን ገድላችንን ፈጸመን ለክብር እንድንበቃ ይራዱናል ፡፡ በመሆኑም የእኛ ሕይወት በኃጢአት ውስጥ መገኘት ሲያሳዝናቸው ፣ በንስሐ ወደ አባታችን መመለሳችን ደግሞ በእጅጉ ያስደስታቸዋል፡፡(ሉቃ.15፡7) ስለዚህ ስለእኛ በቅድስና ሕይወት መဝይላል(1ጢሞ.5፡8)፡፡ እኛ የእነርሱ ቤተሰብ ሆነናልና ቤተሰባዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲሉ ፣ ደካማው ብርቱን እንዲረዳ ቅዱሳን መላእክትም እኛን ለመርዳት ይተጋሉ፡፡ ነገር ግን የእነርሱ እርዳታ ለእኛ የሚፈጸምልን ተራዳኢነታቸውንና ምክራቸውን የተቀበልን እንደሆን ብቻ ነው ፡፡ ምክንያቱም እነርሱም እንደ አምላካቸው በእኛ ነጻ ፈቃድ ውስጥ ጣልቃ አይገቡምና ፡፡ እንዲህም ስለሆነ የሎጥ ሚስት ምንም እንኳ በመልአኩ እጅ ብትያዝም ለመልአኩ ቃል ባለመታዘዙዋና ለመዳን ባለመፍቀዱዋ የጨው ሐውልት ሆና ቀርታለች(ዘፍ.19፡26) ፡፡ በእርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ “በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ መተላለፍና አለመታዘዝ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ..”(ዕብ.2፡2) በማለት እንደገለጠልን እግዚአብሔር ለላከው መልአክ አለመታዘዝ ታላቅ የሆነ ቅጣትን ማምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ልጆቹዋ የመላእክትን ተራዳኢነት አውቀው እንዲጠቀሙና የመንግሥቱ ወራሾች ለመሆን እንዲበቁ ስትል ለቅዱሳን መላእክት የመታሰቢያ ቀን በመስጠት በእነርሱ የምናገኛቸውን እርዳታዎች እንዲታወሱ ታደርጋለች ፡፡

በዚህም መሠረት በህዳር ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ሲመት በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች ፡፡ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ ህዳር 12 ቀን ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በኢዮር ባለችው በአራተኛይቷ ከተማ በሚኖሩት ኃይላት እና በአሥሩ ነገደ መላእክት ላይ አለቃ ሆኖ የተሾመበት ቀን ነው ፡፡እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ ገፍፎ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል፡፡(ይህን ሁለተኛውን ሹመት ያገኘው በሚያዚያ 2 እንደሆነ አክሲማሮስ በሚባለው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ አናገኛለን፡፡)

የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው ፡፡ ይህም እንደሆነ እንድንረዳ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለውን እስራኤል ዘሥጋን ሲራዳና ሲጠብቅ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን ፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ በኢያሪኮ ምድረ በዳ እንደተገለጠለት “… ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ ? አለው ፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ”(ኢያ.5፡13) ይለናል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ ሲያወጣቸው ይመራቸው የነበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነበር ፡፡ ሹመቱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም በመሆኑ ስለ እነርሱ ዲያብሎስ ይዋጋው ፣ በጸሎትም ይራዳቸው ነበር ፡፡ ነገር ግን ኃጢአት ሠርተው ሲያገኛቸው ለእግዚአብሔር አድልቶ ኃጢአተኞችን ስለሚቀጣ እግዚአብሔር ሕዝቡን “በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት”(ዘጸ.23፡21)ብሎ አስጠንቅቋቸው ነበር ፡፡ ይህም ቅዱስ ሚካኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙን ያስረዳናል ፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሕዝበ እስራኤልን ይራዳቸው የነበረው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ አያረጋግጥም የሚል ካለ “መልአክ” የተባለው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ነቢዩ ዳንኤል በተላከ ጊዜ ገልጦልን እናገኛለን፡- ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ቅዱስ ሚካኤል ስለመሾሙ ሲመሰክር “በእውነት በመጽሐፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም”(ዳን.10፡21)ብሎአል፡፡ ስለዚህም ለኢያሱ የተገለጠውና እስራኤላውያንንም የመራው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን እንረዳለን ፡፡

የቅዱስ ሚካኤል አለቅነት በሐዲስ ኪዳንም አንደሚቀጥል ይህ ነቢይ በትንቢቱ “በዚያ ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ ሚካኤል ይነሣል..”(ዳን.12፡1) በማለት ተናግሮለታል ፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሚካኤል እኛን ከሰይጣን አሽክላና ወጥመድ ይጠብቀንና በጸሎቱ በእግዚአብሔር ፊት ይቆምልን ዘንድ በእኛም ላይ ሹም ነው ፡፡ ምክንያቱም እኛ የእግዚአብሔር ሕዝቦችና የርስቱ ወራሾች ነንና፡፡

እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መሾሙ እጅግ ትሑትና ስለመንጎቹን ነፍሱን እንኳ አሳልፎ እስከመስጠት ደርሶ ስለሚወዳቸው ነበር፡፡(ዘኁል.12፡3፤ዘጸአ.32፡32) በሕዝቡም ላይ እርሱን መሾሙ እንዲሠለጥንባቸው ወይም እንዲገዛቸው ሳይሆን በትምህርቱና በጸሎቱ እነርሱን እንዲቤዣቸው ነው ፡፡ እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለሙሴ ሲመሰክር “እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው”አለ፡፡ (የሐዋ.7፡35) እንዲሁ ቅዱስ ሚካኤል ነው ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል እጅግ ትሑትና ለሠራዊቱ ተቆርቋሪ የሆነ መልአክ በመሆኑ በመላእክትና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ተሾመ ፡፡ በመላእክትና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙ ልክ እንደ ሙሴ በእነርሱ ላይ ሊሠለጥንባቸው ወይም ሊገዛቸው ሳይሆን መላእክትን ሊመራ ፣ እኛን ደግሞ ከሰይጣን ጥቃት ሊጠብቀንና በጸሎቱ ሊራዳን ነው (ይሁዳ.12) ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱሳን መላእክት እኛን እንደሚጠብቁና እንደሚራዱ እንዲሁም ስለእኛ በፊቱ አንደሚቆሙ ሲያስተምረን“ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ስንኳ እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ሁል ጊዜ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ”(ማቴ.18፡10) ብሎናል ፡፡ እኛን ይጠብቁ ዘንድ የተሰጡን ቅዱሳን መላእክት ስለእኛ እንዲህ የሚቆረቆሩና ስለመዳናችን የሚተጉ ከሆነ በቅድስናው ልቆ የመላእክት አለቃ ሆኖ የተሾመው ቅዱስ ሚካኤል እንዴት ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ይበልጥ አይቆም?(ሉቃ.13፡6-9) እንዴትስ በተሰጠው ሥልጣንና ኃይል አይረዳን?(መዝ.33፡7) እርሱ “ስለሕዝብህ ልጆች የሚቆመው”መባሉም እኛን በጸሎቱና በተራዳኢነቱ የጽድቅ ሕይወታችንን በሚገባ እንድናከናውን እንደሚራዳን የሚያሳይ ኃይለ ቃል ነው ፡፡

የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል ጸሎቱና በረከቱ በእኛ ላይ ለዘለዓለሙ ይደርብን አሜን ፡፡
ከማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ የተወሰደ

20111221

እንኳን ለአባታችን ኣባ ሳሙኤል የእረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ


እንኳን ለአባታችን ኣባ ሳሙኤል የእረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ አባታችን አባ ሳሙኤል ዘደብረ ዋሊ (ዋልድባ) የተባሉ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ኣባታቸው እስጢፋኖስ እናታቸው ዓመተ ማርያም ይባላሉ:: ትውልዳቸው አክሱም ሽሬ አካባቢ ተወለዱ በኋላም አባታቸውና እናታቸው ስለሞቱባቸው ወደ ገዳም ሄደው ገቡ በዚህም ጊዜ በመንፈሳዊ ትምህርታቸው ላቁ (ጎለመሱ) ተነስተውም ወደ ደብረ መንኮል ገዳም ገቡና ከአባ አድኃኒ ከተባሉ አባት መነኮሱ በዚህም ገዳም ኢይበልዕ ዘእንበለ ሐምል ይለዋል ከጎመን በስተቀር ሌላ ምግብ አይበሉም ነበርና ሲሰግዱም እግራቸው እስኪአብጥ ድረስ ይሰግዱ ነበር። በጾመ ፵ ጊዜም ፵ መአልትና ፵ ሌሊት ምንም ሳይቀምሱ ቆዩ በዚህም ጊዜ ብዙ አናብስት ተሰብስበው ወደ እሳቸው መጡና ግማሾቹም ለእሳቸው እንደፈረስ መሄጃ ግማሾቹም ለቅዱሳን መጻህፍትቶቻቸው መጫኛ እንዲሆኑ የረገጡትን መሬት እየላሱ እንዲኖሩ ታዘዙ። በዚህ ዓይነት ኑሮ ሲኖሩ ወደ ዋልድባ ገዳም ገብተው ገዳሙን አቀኑ መሰረቱ በዋልድባ ገዳም ሲጸልዩ ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ መንበሩን ሲያጥኑ ተገለጸላቸው ከዚህም ሌላ እሳቸው ቅዳሴ ገብተው ቅዳሴ ማርያምን ሲቀድሱም ሆነ ሲደግሙ ከመሬት አንድ ክንድ ከፍ ብለው መሬት ለቀው ይቆሙ ነበር ለእሳቸው ግን አይታወቃቸውም ነበር ከብቃታቸው ብዛት የተነሳ ሌላው ደግሞ ከፍቅራቸው ጽናት የተነሳ ቅዳሴዋንና ውዳሴዋን በቀን በቀን በእድሜዋ ልክ ፷፬ ጊዜ ሲደግሙ ከ፪ ክንድ በላይ ከመሬት ይለቁ ነበር ከሰማይ የወርቅ ጽዋ ወርዶላቸው የቀድሱበት ነበር አባ ሳሙኤል ዋልድባን እንደመሶብ በእጃቸው ይዘው አስባርከዋታል የበረከት ሀገር አንድትሆን ዛሬ በዋልድባ ረሐብ የለም ቅዳሴ ማርያም ሳይደግም የሚውል መነኩሴ የለም አባ ሳሙኤል በዋልድባ ሁነው አባ አንበሳ በአዘሎ ሁነው አባ ብንያም በግብጽ ሁነው ሲጸልዩ በመንፈስ ይተያዩ ነበርና ተቀጣጥረው ፫ቱም በአንበሳ ላይ ተቀምጠው ወደ ምድረ ከብድ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ በረከትን ለማግኘት ሄዱ።አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ እረፍታቸው ታህሣስ፲፪ ቀን ነው ። የአባታችን ያባ ሳሙኤል አምላክ ይጠብቀን ረድኤት በርከታቸው በኛ በልጆቻቸው ላይ ይደርብን አሜን!!!

ታላቁ ፍጥጫ part1 በመምህር ምህረተአብ አሰፋ

ታላቁ ፍጥጫ part 2 በመምህር ምህረተ አብ አሰፋ

ሁለት ነገር ያስፈራኛል አንድ ነገር ያስተምረኛል በ መምህር ምህረተአብ አሰፋ

የአባ ዮሐንስ ኀፂር ሕይወት -ክፍል 1

ዮሐንስ ሐፂር

ዮሐንስ ሐፂር በላይኛው ግብጽ ቴባን በምትባል መንደር በ339 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወደ ገዳም አስቄጥስ የገባው በልጅነቱ ሲሆን ያን ጊዜ አበምኔቱ አባ ባሞይ ይባል ነበር፡፡ አባ ዮሐንስ በተመሥጦው እና በታዛዥነቱ የታወቀ አባት ነበር፡፡ በመጀመርያው የአስቄጥስ ጥፋት ጊዜ ገዳሙን ትቶ ወደ ቁልዝም ተጓዘ፡፡ ያረፈውም በዚያ ነው፡፡
የዮሐንስ ሐጺርን ትምህርቶች ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ፡፡

1. የጠላቱን ከተማ ለመቆጣጠር የዘመተ ንጉሥ አስቀድሞ የውኃውን መንገድ ይዘጋል፣ የእህሉንም መግቢያ ይይዛል፡፡ ያን ጊዜ ጠላቶቹ ይራባሉ፣ ይጠማሉ፡፡ በመጨረሻም እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡ የነፍስን ፆር ለማሸነፍም በተመሳሳይ መንገድ መጠቀም ይገባል፡፡ አንድ ሰው በጾምና በረኃብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይዳከማሉ፡፡

2. እኔ በትልቅ ዋርካ ሥር የተቀመጠንና አራዊት ሊጣሉት የመጣን ሰው እመስላለሁ፡፡ ሊቋቋማቸው እንደማይችል ከተረዳ ሸሽቶ ወደ ዛፉ በመውጣት ነፍሱን ያድናል፡፡ በእኔም የተፈጸመው ይኼው ነው፡፡ በበዓቴ ተቀምጬ ክፉ ሃሳቦች ሊቃወሙኝ ሲመጡ፣ ልቋቋማቸው እንደማልችል ባወቅኩ ጊዜ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ሸሽቼ እመሽጋለሁ፡፡ በዚያም ከጠላቶቼ ፍላፃ እድናለሁ፡፡

ዮሐንስ ሐፂር
3. መለወጥ የምትፈልግን ነፍስ በተመለከተ አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- በአንዲት ከተማ ውስጥ ብዙ ወዳጆች የነበሯት አንዲት አመንዝራ ሴት ነበረች፡፡ ከገዥዎቹ አንዱ ቀረባትና ‹መልካም ሴት ለመሆን ቃል ግቢልኝና አገባሻለሁ› አላት፡፡ እርሷም ቃል ገባችለትና ተጋቡ፡፡ ወደ ቤቱም ወሰዳት፡፡ የቀድሞ አፍቃሪዎቿ ያቺን ሴት ፈለጓት፣ እርስ በርሳቸውም ‹ያ ልዑል ወደ ቤቱ ወስዷታል፤ ወደ ቤቱ ብንሄድ ይቀጣናል፡፡ ነገር ግን በጓሮ በኩል እንሂድ፣ ለርሷም እናፏጭላት፣ የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ከድርሱ ወርዳ ወደኛ ትመጣለች፣በዚህም ያለ ችግር እናገኛታለን› ተባባሉ፡፡ ወደ ቤቷም ጓሮ ተጉዘው ያፏጩ ጀመር፡፡ እርሷ ግን የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ጆሮዎቿን ደፈነች፡፡ ወደ ውስጣዊው እልፍኝም ገባች፡፡ በሩንም ጥርቅም አድርጋ ዘጋች፡፡ ይህቺ ሴት የኛ ነፍስ ምሳሌ ናት፡፡ ወዳጆቿ የተባሉም ፈተናዎቿ ናቸው፤ ገዥ የተባለውም ክርስቶስ ነው፣ እልፍኝ የተባለውም ዘለዓለማዊው ቤት ነው፡፡ እነዚያ የሚያፏጩት ክፉዎች አጋንንት ናቸው፤ ነገር ግን ነፍስ ሁልጊዝም በክርስቶስ አምባነት ትሸሸጋዋለች፡፡

4. አባ ዮሐንስ ልቡናው ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበረ ምድራዊ ነገሮችን ይዘነጋ ነበር፡፡ አንድ ቀን አንድ ወንድም ቅርጫት ሊወስድ ወደ አባ ዮሐንስ በኣት መጣ፡፡ አባ ዮሐንስም ምን ፈልጐ እንደሆነ ጠየቀው፡፡ ያም ወንድም ‹ቅርጫት ፈልጌ ነው› አለው፡፡ አባ ዮሐንስ ወደ በኣቱ ተመለሰና ዘንግቶት ወደ ሽመና ሥራው አመራ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ያ ወንድም አንኳኳ፣ አባ ዮሐንስም ወጥቶ ‹ምን ፈልገህ ነው› አለው ‹ቅርጫት ስጠኝ ብየህ ነበር› ሲል መለሰለት፡፡ ተመልሶ ወደ በኣቱ ሲገባ ልቡናው በሰማያዊ ነገር ስለተመሰጠ ዘንግቶት ወደ ሽመናው ሥራ እንደገና ገባ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ያ ወንድም ሲያንኳኳ አባ ዮሐንስ ተመልሶ ወጣና ‹ምን ፈልገህ ነው?› አለው፡፡ ‹ቅርጫት ስጠኝ ብየህ ነበር› አለና መለሰለት፡፡ አባ ዮሐንስም እጁን ይዞ እየጐተተ ወደ በኣቱ አስገባውና ‹ቅርጫት ከፈለግህ ያዝና ሂድ፣ በእውነቱ እንዲህ ላሉት ነገሮች እኔ ጊዜ የለኝም› አለው፡፡

5. አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ አባ ዮሐንስ ሐፂር በኣት መጣና ሥራውን እያየ ያመሰግነው ጀምር፡፡ አባ ዮሐንስ ዝም አለውና ገመድ መሥራቱን ቀጠለ፡፡ እንግዳውም እንደገና ወሬውን ቀጠለ፣ አባ ዮሐንስም ጸጥ አለው፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ እንግዳው ወሬ ሲያበዛ፡፡ ‹አንተ ወደ በኣቴ በመግባትህ እግዚአብሔር ወጥቶ ሄደ› ብሎ ተናገረው፡፡

6. አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- ‹የብሕትውናን ኑሮ በከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነበረ፡፡ ያ ሰው በከተማው ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውና ባለዝናም ነበር፡፡ አንድ አረጋዊ አባት ከማረፉ በፊት ያንን ሰው ሊያየው እንደሚፈልግ ለዚያ ሰው ጥሪ ደረሰው፡፡ ያም ሰው በቀን ከተጓዝኩ ሰዎች ስለሚከተሉኝ ለኔ የተለየ ክብር ይሰጡኛል ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህም በሌሊት ሰው ሳያየው ለመጓዝ ወሰነ፡፡ በመሸ ጊዜም አሁን ማንም አያየኝም ብሎ ተነሣና ጉዞ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ሁለት መላእክት ታዝዘው መብራተ ይዘው መንገዱን ይመሩት ነበር፡፡ ይህንን የተመለከቱ የከተማው ሰዎች ወደ እርሱ ተሰባሰቡ፣ መላ ከተማው ያንን የመላእክት ብርሃን እያየ ከኋላ ተከተለው፡፡ ከክብር በሸሸ ቁጥር የበለጠ ክብርን አገኘ፡፡ በዚህም ‹ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ከፍ ይላል› የሚለው የወንጌል ቃል ተፈጸመ፡፡ (ሉቃ. 14.11)

7. አባ ጴሜን አባ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ መናገሩን ገልጧል ‹ቅዱሳን በአንድ ቦታ የበቀሉ ዛፎችን ይመስላሉ፡፡ ከአንድ ምንጭ ጠጥተው፣ ልዩ ልዩ ዓይነት ፍሬ ያፈራሉ፡፡ የአንድ ቅዱስ ሥራ ከሌላው ይለያል፣ ነገር ግን በሁሉም አድሮ የሚሠራው አንድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
ከ
ዲያቆን መልአኩ እዘዘው የኔነህ

የቅዱሳን በረከት ይደርብን