በክፍል አንድና በክፍል ሁለት ትምህርታችን የመላእክትን አማላጅነት በተለያየ መንገድ ተመልክተናል፡፡ እነዚያን ያላነበባችሁ በፌስቡክ ኖት ውስጥ ያኖርኩአቸው በመሆኑ ያንን በመክፈት ማንበብ እንደምትችሉ ለመጠቆም እወዳለሁ!
ሦስተኛውን ክፍል እነሆ፡-
‹‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ›› ያለው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አስተምሯል፡፡ /መዝ77.2/ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የመላእክትን አማላጅነት የሚያሳይ ነው፡፡
ሙሉ የወንጌሉ ቃል ከዚህ ቀጥሎ የምናነበው ሲሆን ነጥቦቹን አንድ በአንድ እንመለከታለን፡፡
“ይህንም ምሳሌ አለ። ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። የወይን አትክልት ሠራተኛውንም። እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። እርሱ ግን መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት።ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው።” /ሉቃ13।6-9/
ይህን ቃል ጽፎ ያቆየልን ሐዋርያ ቅዱስ ሉቃስ ቢሆንም ትምህርቱን ያስተማረው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ይህንም ምሳሌ አለ›› ብሎ ታሪኩን በመጀመሩ ትምህርቱ ምሳሌያዊ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም፡፡
የበለሲቱ ጌታ /ባለቤት/ ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ፍሬ ቢፈልግባት ምንም ስላላገኘባት እንድትቆረጥ ለሠራተኛው ጥብቅ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ሠራተኛው በፍጥነት ሊቆርጣት ይችል ነበር፡፡ ያን ቢያደርግም በጌታው ዘንድ ሊመሰገን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የታዘዘውን አድርጓልና፡፡
ነገር ግን ጌታውን ‹‹በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት›› በማለት ስለ በለሲቱ ለመነላት፡፡ አማለዳት ማለት ነው፡፡ ለሌላ ወገን የሚደረግ ልመና ምልጃ ነውና፡፡ የሚገርመው ደግሞ በለሲቱ እንዲለምንላት አልተማጸነችም፡፡ ሠራተኛው በራሱ ደግነት በፈቃዱ ተነሣስቶ ለመነላት እንጂ፡፡ ብትለምነው ደግሞ የበለጠ ሊያደርግ እንደሚችል መረዳት አያዳግትም፡፡ ሊያማልድ ያልተዘጋጀ ወይም ያላሰብ ሰው እንኳን እባክህ አማልደን ብለው ሲልኩት እምቢ እንደማይል ሁሉ ይህ ሠራተኛ ቢለመን የበለጠ ሊያደርግ መቻሉ እሙን ነው፡፡
የበለሲቱም ጌታ የቀጠርኩህ እንድትታዘዘኝ እንጂ እንድትለምነኝ አይደለም ሳይል የሠራተኛውን ምልጃ ተቀበለ፡፡ ይህም ምልጃ ተቀባይ ጌታ መሆኑን ያሳያል፡፡
ምሳሌው እንዴት እንደሚተረጎም እንመልከት፡- የበለሷ ጌታ /ባለቤት/ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ በለሲቱ ደግሞ እስራእላውያንን ቀጥሎም የሰውን ዘር በሙሉ ያመለክታል፡፡ ሠራተኛ የተባለውም ሰውን የሚጠብቅ መልአክ /ዑቃቢ መልአክ/ ነው፡፡ ከበለሲቱ በተስፋ የተጠበቀው ፍሬ ደግሞ ከሰው ዘር በሙሉ ፈጣሪ የሚፈልገው የቀና ሃይማኖትና መልካም ምግባርን ነው፡፡ ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ፍሬ ማጣቱ ፈጣሪ በታዳጊነት፣ በወጣትነትና በጎልማስነት ጊዜ ሁሉ ፍሬ እንደሚፈልግብን ያሳያል፡፡ ‹‹ቁረጣት›› ማለቱ ፍሬ ሲያጣብን ያለ ዕድሜም መቀሠፍ እንዳለና ሞት እንደሚፈረድብን ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ሠራተኛ ለበለሲቱ እንደለመነላት መላእክትም ለእኛ እንደሚለምኑልን እንደሚያማልዱን ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን መመልከት አለብን፡፡ ይህን ካልተቀበልን ምን ብለን ልንተረጉመው ነው? ‹‹ቅዱስ ጠባቂ›› የሚባል መልአክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ /ዳን4।13፤4।23/ እንዲጠብቁንም ያዘዛቸው ፈጣሪ ነው፡፡ ‹‹መላእክቱን ስለ አንተ ያዛቸዋል፡፡›› ተብሏልና፡፡ /መዝ90।11/
ይህ ምሳሌያዊ ትምህርት በርካታ መልእክቶችን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ቃልና ዐረፍተ ነገርም ብዙ ምሥጢር ይዟል፡፡ የእኛ ርእስ ግን ስለ ምልጃ ስለሆነ በዚህ እንወሰናለን፡፡ ይሁን እንጂ ጎላ ያለ ጥያቄ መልሶ ለማለፍ ያህል አንድ ሰው የበለሲቱ ባለቤት ‹‹ትቆረጥ›› ሲል ሠራተኛው ደግሞ ‹‹በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት›› ማለቱ ለበለሲቱ ከባለቤቱ ይልቅ ሠራተኛው ያዘነላት አያስመስልም? ሊል ይችላል፡፡
ለበለሲቱ ከሠራተኛው ይልቅ ያዘነላት ጌታዋ ነው እንጂ ሠራተኛው አይደለም፡፡ እንዴት ቢባል ጌታዋ ከአንድም ሦስት ጊዜ ሳይቆርጣት አልፎአታል፡፡ በተጨማሪም ሠራተኛው የለመነላት ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እንዲያው ከዚያ በኋላ ካላፈራች ‹‹ትቆርጣታለህ›› ሲል ተናገረ፡፡ ጌታዋ ለሦስት ጊዜ የታገሣትን እርሱ ግን አንዴ ከለመነላት በኋላ ብትቆረጥም ቅር እንደማይለው አስረዳ፡፡ ታዲያ ከጌታዋ ይልቅ እርሱ ራራ ለማለት እንዴት ይቻላል? በዚያውም ላይ ያ ሠራተኛ ቢለምንላትም ይቅር ያላት ግን ጌታዋ መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር እንዲህ አዝኖ የሚያማልዳትን ሠራተኛ ያዘዘላት እኮ ጌታዋ ነው፡፡ በመጨረሻ ትምህርቱ ምሳሌያዊ ነው፡፡ ‹‹ቁረጣት›› ያለው ጌታዋ የፈጣሪ ምሳሌ እንደመሆኑ መጠን ሠራተኛው የሚያቀርብለትን የምልጃ ጥያቄ አስቀድሞ ያውቃልና በለሲቱ እንደማትቆረጥ ያውቅ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እርሱ በበለሲቷ ላይ ያለውን የማዘዝ ሙሉ ሥልጣን እና የሠራተኛውን ማለትም የጠባቂ መልአኩን የማማለድ ሥራ ሊያሳይ በሚችል መንገድ ምሳሌውን እርሱ ባወቀ መስሎ ተናገረ፡፡
-በቃል የሚጠና ጥቅስ ሉቃ 13।6-9
-ሐሳብ - የበለሲቷ ምሳሌ
-ትምህርት - በሠራተኛው ልመና አንጻር የመላእክትን አማላጅነት ማሳየት
ይቆየን!
የቅዱሳን መላእክት አማላጅነትና ተራዳኢነት የፈጣሪ ቸርነት አይለየን!