20110115

1. ምስጢረ ሥላሴ


ሥላሴ ማለት የግእዝ አጠራር ነው። ትርጉሙ ሦስትነት ወይም ሥሉስነት ማለት ነው። የምስጢረ ሥላሴ ሁኔታ በዘመነ ብሉይ እንደ አሁኑ /ዘመነ ሐዲስ/ ግልጽ አልነበረም። ይህ ለብዙ ዘመናት ለጥቂቶች ግልጽ ለብዙዎች ግን ሥውር ሆኖ የነበረው ምስጢር ጐልቶ የወጣው በክርስቶስ መገለጥ ወይም ሥጋችንን ለብሶ ወደዚህ ዓለም መምጣት ነው። ጌታ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ በማያሻማ መልኩ ተገልጧል /ማቴ 3፥16/::

ሥላሴ ስንት ናቸው? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ሥላሴ አንድም ሦስትም ይሆናሉ /ናቸው/ የሚል ነው። ይህን መልስ ተከትሎ የሚመጣ ጥያቄም አለ እሱም ''ሥላሴ በምን አንድ ይሆናሉ በምን ሦስት ይሆናሉ'' የሚል ነው። የሁሉም መልስ ቀጥሎ ያለው ነው።

የሥላሴ አንድነት

ስለ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ስናነሳ ቀድመን የምንመለከተው ''አንድነትን'' ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ለአንድነታቸውና ለሦስትነታቸው መቀዳደም ኑሮበት ሳይሆን የቁጥር መሠረት አንድ ስለሆነ በዝያው ለመጀመር ነው /እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ/ ሥላሴ አንድ ይሆናሉ በምን? በዐይነ ሥጋ የማይታይ የሰው አዕምሮ የማይመረምረው፣ የሰው ሕሊና አስሶ የማይደርስበት ከዓለም በፊት የነበረ በማዕከለ ዓለም ያለ፣ ዓለምን ኣሳልፎ የሚኖር አምላክ መኖሩን እናምናለን። እርሱም ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ነው።

በምን አንድ ይሆናል ለሚለውም፦

1. በመለኮት:- መለኮት ማለት "መለከ - ገዛ" ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሆኖ ''ግዛት'' ማለት ነው። በእብራይስጥም ማልኮት ይባላል። እንግዲህ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኮት ይህም ማለት በግዛት በመንግስት አንድ ናቸው። ለዚህም ቅ/መጽሐፍና አበው ተባብረውበታል።

- ''መንግስትህ የዘለዓለም መንግስት ናት ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው::" /መዝ 144፥13/ /መዝ 145፥10/ /መዝ 73፥12/
/ዳን 4፦3/ /ዳን 4፥34/ /1ተስሎ 2፥12/
- "በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና::" /ቈላስ 2፥9/
- የመለኮቱ ኃይል በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰለ ---ሁሉን ስጠን /2ጴጥ1፥3/
እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ''መለኮቱ'' አለ እንጂ ''መለኮቶች'' በማለት አላበዛውም።

አበው ይህን መነሻ በማድረግ ያሉትንም እናስከትላለን::

+ ዮሐንስ ዘእስክንድርያ ''እስመ ምስጢረ ሥላሴ ይትሌለይ በአካላት ወኢይትሌለይ በመለኮት። ወመለኮቶሙስ አሐዱ ውእቱ። አኮ ከመ ዘርሁቃን ይትቃረቡ በበይናቲሆሙ በሱታፌ ተራክቦ አላ እሁዛን በጽምረተ አሐዱ መለኮት" ብሏል።

+ ሚናስ ዘእስክንድርያ:- "መለኮትኒ ይትዐወቅ ከመውእቱ ያኅብር ቅድስተ ሥላሴ።"

+ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ:- "መጻሕፍትሒ ቅዱሳት ያቤይና ከመውእቱ አሐዱ መለኮት'' ካለ በኋላ "ወበዝንቱ አዕመርነ ከመ አሐዱ ውእቱ መለኮት ዘቦቱ ሠለስቱ አካላት'' ብሏል።

+ ዲዮናስዮስ ዘእስክንድርያ:- "ይሤለሱ በአካላት ወይትዋሐዱ በመለኮት ወሶበሂ ንሬሲ ቅድስተ ሥላሴ ፍሉጣነ መለኮት ዘከመ አካላቲሆሙ ንትአመን እምነተ ሰይጣናዌ::'' ብሏል:: ሊቁ በተጨማሪም ''ንህነሰ ከመዝ ንሰግድ ለአሐዱ አምላክ ባሕቲቱ ወንትአመን በአሐዱ መለኮት ዘሠለስቱ አካላት ወኢንበውእ ኅበ ከፊለ መለኮት ወመንግስት'' ሲል አስተምሯል።

እነዚህ ደጋግ አባቶች እግዚአብሔር በመለኮት አንድ መሆኑ በማያሻማ መንገዱ አመስጥረው አስቀምጠውታል።

ርዕሱን ከማጠቃለላችን በፊት ከቤተክርስቲያን አባቶች ውጭ የሆነ ዋርፊልድ የተባለ ፀሓፊ ያለውን እንጥቀስ።

ዋርፊልድ ስለ ቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት የሚከተለውን ጽፏል:: ''መቼም ቢሆን ቃላት ነገረ-እግዚአብሔርን በትክክል ሊገልጹልን አይችሉም። ቢሆንም ግን አንድን ነገር ለማብራራት ሌላ አማራጭ ስለሌለን የትም አንሄድም ''አንድና እውነተኛ አምላክ አለ። ይህም አንድ አምላክ ሦስት እኲል አካላት በመለኮት አንድ የሁኑ በአካል ግን የተለዩ አሉት'' ብሏል። /ዋርፊልድ የቲኦሎጂ ትምህርት ቢኖረውም ዓለማዊ ፀሓፊ ነው።/

ቤተክርስቲያን ትምህርት የተካኑት አባቶቻችን ሃይማኖታቸውን ይህን ይመስላል።

2. በባሕርይ:- ባሕርይ ማለት "ብሕረ ተንጣለለ፥ ሰፋ፥ ዘረጋ" ከሚለው ግስ የወጣ ነው። በቲኦሎጂ /በነገረ መለኮት/ ቋንቋ ሲፈታም ባሕርይ ማለት ሥርው፥ ነቅዕ አዋሃጅ /የሚያዋሕድ/ አስተገባኢ ማለት ነው። ባሕርይ አካል ሥራውን የሚሠራበት መሣሪያ ነው። አባቶች 'አንዳርጌ ሰብሰቤ' እንደማለት ነው ሲሉ "አስተጋባኢ" ብለውታል። ባሕርይና አካል እንደ አጽቅና እንደ ሥር አንድ ናቸው አይለያዩም አንዱ ያለ አንዱ መኖር አይችልም።

+ ባሕርይ ሥር፥ ምንጭ፥ አዋሐጅ የተባው ለምንድን ነው? ቢባል ሥርና ምንጭ ከእርሱ ለሚበቅለውና ለሚመነጨው ወይም ለሚወጣው ነገር ጥንትና መሠረት እንደሆነ ሁሉ ባሕርይም የአካልና የግብር የስምም መሠረት ነውና ሦስቱን አካላት የሚያስገኝና የሚያዋሕድ ስለሆነ ነው። እዚህ ላይ ባሕርይ መሠረት አስገኝ ስለተባለ ባሕርይ ከአካል ከስምና ከግብር ባነጋገር እንጂ በመኖር የሚቀድም ሆኖ አይደለም። ባነጋገር ግን የቁጥር መሠረት አንድ ስለሆነ ነገርን ከስሩ ለማምጣት 3 ከሚሰኙበት ነገር አንድ የሚሰኙበት ነገር መነሻ ማድረግ ስለሚገባ ነው። በዚህ መሠረት ሥላሴ በባሕርይ አንድ የሚሆኑበት ሥረ-ነገር ምንድን ነው? ያልን እንደሆነ:-

- መፍጠር:- ''አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው:: /መዝ 101፥25/ አሁን የተመለከትነው ጥቅስ ''ምድርን መሠረትህ'' ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው አለ እንጂ::

- ምድርን መሠረታችሁ የእጃችሁ ሥራ አላለም።

- ከዚህ በተጨማሪ ሥላሴ በመፍጠር ባሕርያቸው አንድ እንደሆኑ ብዙ መጥቀስ ቢቻልም ጥቂቱን ብቻ እነሆ (ዘፍ 1፥1) (ኢሳ 44፥24) (ኢሳ 40፥22) (ኢሳ 66፥2) (ኤር 10፥12) (ኤር 51፥15)

- ከዚህ በተጨማሪ ሥላሴ በባሕርይ አንድ የሚሆኑባቸው ነገሮች

መስጠት፣ መንሳት፣ መግደል፣ ማዳን ባጠቃላይ ሁሉም ቻይነት፥ ግዛት ጥበብ፥ ዕውቀት ምክር፥ ሥምረት እንዲህ ያለ ስመኛ ቃል ሁሉ የባሕርይ አንድነታቸውን ያሳያል። ይህም በመሆኑ ቅድምናቸውና ዕሪናቸው አንድ ነው። መቅደም መቀዳደም፣ መብለጥ መበላለጥ የለባቸውም። ይህ ሁሉ የሆነው ባሕርያቸው አንድ በመሆኑ ነው፦

ቅ/ቄርሎስ ''ኢይቀድም አሐዱ እምካልዑ : ወካልኡ እምሣልሱ አሐቲ ቅድምናሆሙ ለሥላሴ። ኢሀሎ አብ ዘመነ ዘእንበለ ወልዱ ወመንፈሱ አሐተ ስዓተ-ወኢ ከመ-ቅጽ በተዓይን። ሥላሴ ዕሪት ዘእንበለ ፍልጠት::

3. በኅልውና:- ሕልውና ማለት "ነዋሪነት፥ ኑሮ፥ አነዋወር" ማለት ነው። በነገረ መለኮት ቋንቋ አፈታት ግን አብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ኅልው ሆኖ፣ ወልድም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ኅልው ሆኖ፣ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ኀልው ሆኖ በመኖር አንድ ናቸው ማለት ነው። በሌላ አባባልም ህልውና ሦስትነታቸውን ሳይጠቀልለው፣ ሦስትነትም አንድነታቸውን ህልውናውን ሳይከፍለው አንዱ ከአንዱ ጋራ ተገናዝቦ ባንድነት መኖር ነው። /በኲነት ርዕሳችን የበለጠ ይብራራል/

- ጌታ ስለ ኅልውናቸው አንድነት የሚከተለውን ብሏል። ''ኢተአምንሁ ከመ አነ በአብ ወአብ ብየ'' /ዮሐ 14፥9-11/

+ ዮሐንስ ዘእስክንድርያ:- "ነአምን እስመ አብ ህልው በወልድ ወበመንፈስ ቅዱስ። ወወልድኒ ኅልው በአብ ወበመንፈስ ቅዱስ፣ ወመንፈስ ቅዱስኒ ህልው በአብ ወበወልድ።" እንዳለ/ የሥላሴ አንድነት እኛ ከምናውቀው ''አንድ'' የተለየ ነው በዚህ አንድነት ውስጥ ሦስትነት አለና ይኸውም የሚከተለው ነው::
. ይቀጥላል