20110429

ከሦስት ሺሕ በላይ ኢአማንያን ዳግመኛ ተወለዱ።

ከሦስት ሺሕ በላይ ኢአማንያን ዳግመኛ ተወለዱ።

በከንባታ ጠንባሮ እና አላባ ሀገረ ስብከት በተካሔደ ሐዋርያዊ ጉዞ ከሦስት ሺሕ ስድስት መቶ በላይ ኢ አማንያን ተጠምቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጅነትን አግኝተዋል።

የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፤ የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር በሸፈነው ሙሉ ወጪ የካቲት 19 ቀን 2003 ዓ.ም በተደረገው ሐዋርያዊ ጉዞ በርካታ ምእመናን ቃለ እግዚአብሔርን ከማግኘታቸው በተጨማሪ የሌላ እምነት ተከታዮችም በመጠመቃቸው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል።

ጉባኤው በተ ደረገባቸው በዱርጊ መንበረ ሰብሐት ቅድስት ማርያምና በእምብኩና ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ሠላሳ አንድ፤ በሀደሮና ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ በኦጆራ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ አንድ ሺሕ ሦስት መቶ ስልሣ አራት በአጠ ቃላይ ሦስት ሺሕ ስድስት መቶ ዘጠና አምስት የሌላ እምነት ተከታይ የነበሩ በብፁዕ አቡነ ቀለምኒጦስ የከንባታ ሀድያ ስልጢ ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ እጅ ተጠምቀዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በዚሁ ወቅት እንደተ ናገሩት፤ የሥላሴን ልጅነት ያገኙትና በፍቅሩ ወደ ቅድስና ስፍራው የመጡት ሁሉ ሦስት መንፈሳዊ ጸጋዎችን ማለትም፤ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ዳግመኛ መወለድን፣ በቅብዓ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ /ዘይት/ መክበርን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበልን አግኝተዋል፡፡

«የእግዚአብሔር ዓላማ ማንም ሰው የመንግሥቱ ወራሽ እንዲሆን ነው፡፡ ዛሬ የተጠመቃችሁትም የእግዚአ ብሔር ልጆች ሆናችኋል» ያሉት ብፁዕነታቸው፣ «የእግዚአብሔር መንግሥትን ለመውረስ የሚያስችላችሁን መልካም ሥራ መሥራት፣ በጸሎትም መትጋት እና በሃይማኖት መጽናት ያስፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆናችሁ ከማኅበረ መላእክት እና ከቅዱሳኑ ስለተቀላቀላችሁ ደስ ይበላችሁ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሥጋዊውም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወታችሁ ትጸልያለች» ብለዋል፡፡

የከንባታ ጠንባሮ አላባ ሃገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ሚካኤል ገብረ ማርያም በበኩ ላቸው፤ ጥምቀቱን ተቀብለው የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ልጅነትን ያገኙት ምእመናን፣ በክርስቲያናዊ ሕይወታቸው መጠንከር፣ በጸሎት መትጋትና መማር እንዳለባቸው አሳስበው ወደፊ ትም፤ «እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው ባላቸው ሙያ ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማገልገል እና በእርሷም የመገልገል መብት አላቸው» ብለዋል፡፡

«በዛሬው ዕለት የተጠመቃችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ከጨለማ ወደ ብርሃን ዘለዓለማዊ ሕይወት ተሸጋግራችኋል፡፡ ስለዚህ መንግሥተ እግዚአብሔርን የሚያስገኝ በጎ ሥራ እንድትሠሩ በጾም በጸሎት ትጉ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለእናንተ የሚገባችሁን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነች» ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ሀገረ ስብከቱ ሕዝቡን በትጋት ለማገልገል ቃል መግባቱን ተናግረዋል፡፡

/ ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ሚያዝያ 1-15 2003 ዓ.ም /