20110215

ወለንኪ ቅዱስ ዮሓንስ ወቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በቃጠሎ ሙሉ ለሙሉ ስለመዉደሙ



ባለፈው አመት ጥር 2002 ዓ.ም ከ አስገራሚው እና ታሪክን በ ሰሩ ወጣቶች ተከብሮ ከዋለው የ ጥምቀት በዓል በኃላ የተሰማው አስደንጋጭና አሳዛኝ ዜና ነበር:: እሱም በምዕራብ ሽዋ ከ አዲስ አበባ 65 ኬ.ሜ እርቆ የሚገኘው የ ወለንኪ ቅዱስ ዮሓንስ ወቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ባልታወቁ ወገኖች ሙሉ ለሙሉ መቃጠል ነበር:: በቃጠሎው ከታቦቱ በስተቀር መላው ቤተ ክርስቲያኑና ንዋየ ቅዱሳት ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል::ይህም ድርጊት በከተማዋና በዙሪያዋ ብሎም በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የተዋህዶ ልጆች እና ሀገራቸዉን የሚወዱ ወገኖችን ያስቆጣ ነበር እኩይ ተግባር ነበር:: በአጭር ጊዜ ዉስጥ ቤተክርስቲያኑ ተሰርቶ ንዋያተ ቅዱሳት ተማልቶ አገልግሎት መስጠት ጀምራል::አሁን ግን ያ ሁሉ አልፎ ቤተክርስቲያንዋ እንደገና አገልግሎት መስጠት ጀምራለች ሁሉን ያከናወነልን እግዚአብሔር ይመስገን:: "የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።" ማቴ 16:18 ግራኝ አህመድም ዮዲት ጉዲት ሁሉም ተዋህዶን ለማጥፋት ሞከሩ አልቻልሙም ይልቁንስ እየሞትን በዛን በመግደል ጽድቅ እንደሌለ በ እርግጥ አሳይተናል ለምሳሌ ፓዉሎስ አንገቱን ተሰየፈ ጴጥሮስም ተሰቀለ ብዙ ቅዱሳን በ ስቃይ እንዳለፉም እናዉቃለን የተዋህዶ ልጆች ዛሬም በ ስቃይ በፈተና ማለፍን ከ አባቶቻችን ተምረናል እና ቀዳሚ በሆነችው ተዋህዶ እንጽና ፍቅርን ያስተማረን የ እግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው እና ክፉን አትፍሩ

20110201

ጻድቁ አባታቺን አቡነ ተክለ ሃይማኖት



አቡነ ተክለኃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ ዓ.ም ታሕሣሥ ፳፬ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ወይም ደስታዋ ማለት ነው፡፡

ወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በአሥራ አምስት ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ /ጌርሎስ/ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ኃሃይማኖት» አለው፡፡ ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡
አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ

«አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡»

/ገድለ ተክለ ኃይማኖት ምዕ ፳፰ ቁ ፪ - ፫

ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ኃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲገልፅ:-

* «እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» /ዕብ. ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ / እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡
* «ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡
* «የአንበሶችን አፍ ዘጉ» ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ /ምዕ ፲፩ ቁ ፴፬ /እንዳለው አባታችንም የአውሬውን ፥ የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጠዋል።
* «ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡
* «ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡

ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁ?» እያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡

በመጨረሻም አባታችን በነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸው ሆነ፡፡ በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችንለእኚህ ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡ እኛንም ከጻድቁ ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡



ስብሐት ለእግዚአብሔር