20121103

ዘማሪት አቦነሽ አድናው ከኪነጥበብ ጋደኞቿ የሽኝት ፕሮግራም ተደረገላት

በትላንትናው ዕለት በተደረገው የእራት ግብዣ ለዘማሪት አቦነሽ አድነው መሸኛ ብዛት ያላቸው አርቲስት ጓደኞቿ በተሰበሰቡበት ንግግር በማድረግ የዘፋኝነት ስራዋን ለቃ ወደ እግዚአብሔር  አመስጋኝነት ወደ ዘማሪነት የተሸጋገረችና ለመጨረሻ ጊዜ የዘፈኑን ዓለም የተወችና ያቆመች መሆኑን ለአርቲስት ጓደኞቿና በዕለቱ ለነበሩት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ተናግራለች። አቦነሽ ስትናገር እኔ ለ24 ዓመት በሙዚቃው አለም አገልግያለሁ ሙዚቃን በጣም እወድ ነበር ሙዚቃ ለኔ ትልቅ ባለውለታዬ ነው አለምን አዙሮ አሣይቶኛል እኔም አድጌበታለሁ ሙዚቃ ለህይወቴ ብዙ አስተዋፅኦ አድርጎልኛል። ኑሬበታለሁ ቤተሰቦቼን ረድቼ ልጆቼን አሣድጌበታለሁ። ግን ዘማሪ መሆንን የተመኘሁትን ያህል ድምፃዊ መሆንን ተመኝቼው አላውቅም ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ልቤ ሸፍቷል ሁል ጊዜ አስበው ነበር ዘማሪ መሆን እግዚአብሔርን ማገልገል የበለጠ ዋጋ ያለው መሆኑን አውቅ ነበር። እናም እግዚአብሔር ይመስገን ተሳካልኝ ሀሣቤ ሞላልኝ ይሄው ዛሬ በምወዳችሁ የጥበብ ጓደኖቼ መካከል ከአሁን በኋላ ዘማሪ ነኝ! ለወደፊትም መፅሀፍ ቅዱስ ቁጥር እየጠቀስኩ ብዙ ስለ እግዚአብሔር ልነግራችሁ እወዳለሁ ስትል ጓደኞቿን ተማጥና ከዘፈን ዓለም መሠናበቷን አብስራለች። በእለቱ የተሰበሰቡት ጓደኞቿም ለአቦነሽ(አቢቲ) ያላቸውን ክብር ገልፀው። በጭብጨባ የስራ መልቀቂያ ፈቃድ ሰጥተው በዘፈን አለም በነበረችበት ጊዜ አብረዋት ስላሣለፉት ስለ ፅባይዋ በጣም ንፁህ ደግ ቅንና ከበፊትም በዘፈን ዓለም ላይ እያለችም ከአፏ የሚወጡት ከአንደበቷ የሚፈልቁት ቃሎቿ የተቀደሱ ክፉ ነገር የማይወጣት የዘፈነችው የሚያምርባት ስትስቅ ስትጫወት ተወዳጅ የሆነች ትሁት በመሆኗ የመረጠችው መንገድ የሚገባትና ጥሩ የእግዚአብሔር አገልጋይ ልትሆን የምትችል መሆኗን በዕለቱ እየተነሡ ምስክርነት ሰጥተዋል። በምሽቱ የእራት ግብዣ ላይ አብረዋት ሲዘምሩ ሲያሸበሽቡ ብሎም በግጥም ስንኝ የቋጠሩላትም አንጋፋ አርቲስቶችም ነበሩ።
ተነሡ ለምስጋና(3)
ለዚህ ላበቃን እንዘምርለት
በዙፉኑ ፊት እንስገድለት!
እያለች አዲስ የሰራችውን መዝሙር በጣፋጭ ድምጿ ስትዘምር ከፊቷ ደስታና ብሩህ ህይወት ይታይባት ነበር።
በዕለቱ ከነበሩት ታላላቅ አርቲስቶች መካከል ታላቋ የኪነ-ጥበብ ሰው አርቲስት አለምፀሃይ ወዳጆ ስለ አቢቲ የሙዚቃ አነሣስና ታሪክ በጥቂቱ እንዲህ ስትል ተደምጣለች።
አቢቲ የተወለደችው በደቡብ ኢትዮጵያ በሃይቆችና ቡታጅራ አዉራጃ በሶዶ ወረዳ ቡኢ በምትባል ትንሽ ገጠር መንደር ሲሆን በጊዜው የነበሩት የሙዚቃ ጥበብ ባለሙያዎች ወደ አቢቲ መንደር ወደ ቡኢ በወረዱበት ጊዜ አቢቲን ለሙዚቃ አጯት። እሷም ሁል ጊዜ በዚህ በኪነጥበብ ሙያ ውስጥ ባለውለታዋ የሆኑትን ኮረኔል ለማ ደምሠውንና አርቲስት አየለ ማሞን ሁልጊዜ ታነሣለች። አቢቲ ገና ሙዚቃን የጀመረችው በድሮው የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡደን ውስጥ ነው ሀ ብላ ሙዚቃን የተቀላቀለችው። ከዚያ በኋላም ባሳተመችው “ባላገሩ” “ባህሌን” በተሰኙ ሲዲዎቿ  ተወዳጀነትን ያተረፈች ሲሆን አቢቲ መቼም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ህይወት ሁላችን አርቲስቶችም ሆንን የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያውቀው ሙዚቃን ደምቃበታለች፣ አለምን ዞራበታለች፣ ታጅባበታለች፣ ተምነሽንሻበታለች በትላልቅ መድረኮች ላይ የመስራት እድል አግኝታበታለች። በዚያም መጠን ደግሞ ተወቅሣበታለች፣ ተከሣበታለች፣ በሬዲዮ ተወግዛበታለች እናም በተለያዩ ሁኔታዎች በማለፍ የሙያ አስተዋፀኦ አበርክታበታለች። አቢቲ ገና ስትጀምር ጀምሮ ከታላላቅ አርቲስቶች ከነ ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ከነ ብዙነሽ በቀለ እና ሌሎችም በነበሩበት የጀመረች በመሆኑ እስከ መጨረሻው በዚህ በአሜሪካም ከታላላቅ አርቲስቶችና ታላላቅ መድረኮችን የማግኘት እድልም አግኝታለች። በግሏ በአቢቲነቷ  በአለም አቀፍ መድረክ እንደነ ኬኔዲ ሴንተር ባሉ ቦታዎች በመገኘት ተጫውታ ሌሎችንም ተከታዮችና አድናቂዎችን ያገኘች አርቲስት ናት።
እግዚአብሔር ለዚህ ካበቃሽ እንግዲህ እኛም ያንቼን እድል ይስጠን እያልን ባለችበት ፀንታ፣እንድትቆይ እየፀለይን እየደገፍናት፤ እያገዝናት የሀሣቧ ተከፋይ እየሆንን እንዳንለያት። እኛንም እንደ እሷ እንዲያበቃን እንፀልያለን። አቢቲ ታመሽ በነበርሽበት ወቅት ድጋሜ ህይወት ከሠጠኽኝ ጌታዬ ለአንት አገልጋይህ እሆናለሁ ባልሽው መሠረት ባገኘሽው ድጋሜ ህይወት አምላክሽን ለማመስገን መልካሙን መንገድ መርጠሻልና ስምሽም ገና ከማለዳው የተሠጠው “የአቦ ነሽ” ነውና አቦዬ ብርታቱን ፅናቱን እንዲሰጡሽ በእኔና በጓደኞችሽ ስም እመኝልሻለሁ በማለት አርቲስት ዓለምፀሃይ ወዳጆ እና ሌሎችም ጓደኞቿ መልካሙን በመመኘት ስትዘምር እየዘመሩ፣ ስታሸበሽብ እያሸበሸቡ፣ ምሽቱን አብረዋት በመሆን ድጋፋቸውን በመስጠት ከእንግዲህ ወዲህ እንደድሮው አብረዋት በአለማዊው መድረክ የማይቆሙ መሆኑን ሲያውቁ የትካዜ መልክ ቢታይባቸውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተክርስቲያን አማኞች በመሆናችን ወደ አንቺ የምንመጣበት አንችን ፈልገን የምንመጣበት መልካም ቦታ ላይ ስለምናገኝሽ እንዳልራቅሽን በመገመት በደስታ ጥያቄሽን መልሠናል መልካሙን ሁሉ ይግጠምሽ ብለዋታል። በእለቱ በነበሩት ወጣት ዘማሪያን መካከል ዘማሪ ቸርነተ ሰናይ ዘማሪ ያሬድ እና የመዝሙር ዜማና የግጥም ደራሲዉ ሊቀ ትጉሃን መኩሪያ ጉግሳና ሰባኪ ቀሲስ ተስፋዬ መቆያ እንዲሁም ዲያቆን ቢኒያም እና ሌሎችም የተገኙ ሲሆን በምሽቱ የተገኙትን አርቲስቶች አመስግነዉ የዛሬዉ ዝግጅት በእናንተ የተዘጋጀ መሸኛ ነዉ።
እኛ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ደግሞ ለእህታችን ለዘማሪት አቦንሽ አድነዉ ኖቬምበር 21.2012 በ 845 ኖርዝ ሃዋርድ ስትሪት አሌክሳንድሪያ ቨርጅኒያ በመናደርገዉ ዝግጅት ላይ በምናዘጋጀዉ የአቀባበል ዝግጅት ላይ እንድትገኙልን እናሳስባለን። በእለቱ ታዋቂ ዘማሪያን ዘርፌ ከበደ፣ ቸርነት ሰናይና ሌሎችም እዉቅ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዘማሪያንና ታዋቂ ሰባኪያን እንዲሁም ህዝበ ክርስቲያኖች የሚገኙ መሆኑን ገልጸዉ ምሽቱን በምርቃት አክትምዋል።
ምንጭ ባዉዛ ጋዜጣ



6 comments:

  1. melkam neber gen men waga alew yehadeshew TEHADESOWCHE gar new.....egzabehar ke tehadesowche yetbekeshe

    ReplyDelete
    Replies
    1. እግዚያብሄር እንኳን ለዚህ አብቃሽ የአቡዬ ስጦታ ነሽና
      አንተ ድግሞ ወሬኛ የስም ላፒስ አልተሳካም በሰው ጸጋ የምትቀና አላዝን ነጠላ ዜማህ አልተደመጠም አልተጣመንም ምቀኛ ምቀኛ ምቀኛ ነህ ከነ ምናምንቴህ

      Delete
  2. Egziabher mechershawn yasamerlat.

    ReplyDelete
  3. And tell her that christianity is not only about singing a song, it's carrying a cross too.

    ReplyDelete
  4. በታላቅ ፍቅሩ የጠራሽ ጌታ እግዚሃብሔር መጨረሻውን ያሳምርልሽ አሜን፡

    ReplyDelete