20120913

ድምጻዊት አቦነሽ አድነው ዘፈን አቁማ ዘማሪት መሆኗን አስታወቀች


"ባላገሩ" በተሰኘው አልበሟ የምትታወቀው ድምጻዊት አቦነሽ አድነው ሙዚቃ ማቆሟን እና ወደ ዘማሪነት መግባቷን ይፋ አደረገች::
ድምጻዊቷ ካሁን በኋላ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስርዓት መሰረት እግዚአብሔርን አመሰግነዋለዉም ብላለች::
"ይህን ዉሳኔ ለመወሰን 5 ኣመታት ያህል ፈጅቶብኛል " ያለችው ድምጻዊቷ "ማታ ማታ ስዘፍን  ቃሉን እራብ ነበር ጠዋት ቤተክርስትያን ለቅዳሴ ባልደርስም ቃሉን ስመቼ ስመለስ ልቤን ያጸናልኝ ነበር " ካለች በኋላ "በአዲሱ አመት አሮጌዉ ማንነቴን ቀይሮ እዚህ በ ቤቱ እድገኝ እና ቆሜ እንድዘመር  እግዚአብሔር ስለረዳኝ አመሰግለዋለው "በማለት
 "አበረታኝ ክንድህ ጌታዬ
አበረታኝ ፍቅርህ አምላኬ
 በስምህ ድኛለው ፀጋህ
በማደሪያህ ሆኘ ስጠራህ "የሚለዉን የዘማሪ ዳግምዊን  መዝሙር ዘምራለች:: ቀሲስ መምህር ተስፋዬ መቆያ አያይዘው እንደተናገሩት የጠፉ ወገኖቻችን ተመልሰው ለጌታ ክበር እንዲዘመሩ ሁላችንም በፍቅር በአንድነት እንቁም የሚል መልክት አስተላልፈዋል::
የቀድሞዋን ድምጻዊት አቦነሽ አድነዉን ምስክርነት የሚያሳየዉን video ይመልከቱ


20120904

በጀርመን የሚገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ማህበር ካህናት አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ጠየቁ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
በጀርመን ሀገር በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ሆነን  በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የአደራ ቃል መሠረት በንጹሐን አባግዕ የተመሰሉ ምዕመናንን ተግተን በመጠበቅ ቤተ ክርስቲያንንም በማገልገል ላይ የምንገኝ የማኅበረ ካህናት የጋራ ያቋም መግለጫ።

በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስቅዱስ እናተን   ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ   የሐሥ ፡20፡28-30



መሪዋና አጽናኞዋ መንፈስቅዱስ የሆነችው ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለያዩ  ዘመናት ብዙ የፈተና ጊዜያትን ተቋቁማ በማለፍ ተወዳዳሪ የማይገኝላት ቤተ ክርስቲያን መሆኗ ለማንም የተሠወረ አይደለም ።
   ለምሳሌም ያህል፦ የዮዲትንና የግራኝን  የመከራ ዘመን ብቻ መጥቀሱ ከበቂ በላይ ነው ማለት ይቻላል ።ወደዝዝር ሁኔታው  ለመግባት አሁን አስፈላጊ ስላልሆነ እናልፈዋለን ። አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት የሰበሰቧት ቤተክርስቲያን  ባሳለፈችው የመከራ ዘመን ሁሉ አንዲት በመሆኗ ችግሩን በአንድነት መንፈስ ተቋቁማ  እስከ አሁን ድረስ ያለምንም ችግር ደርሳለች ።ይችን ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያን ለማዳከም በየጊዜው  ከውስጥም ከውጭም ያልተጠነሰሰ ሴራ የለም በውጭ በኩል ስናይ የምዕራባውያኑ የዕምነት ድርጅቶች ወቅትና ጊዜን በመጠበቅ ልጆቿን ምእመናንን ከጉያዋ እየነጠቁ የነሱን ዕምነት እንደ ህጻናት ወተት ግቶ በማሳደግ በዚች ቤተ ክርስቲያን ላይ በጠላትነት እንዲነሱ ማሰለፍ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሀገሪቱ መንግሥት በየጊዜው  በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ቤተ ክርስቲያኗን እየጎዳት ይገኛል። የሩቁን ትተን የቅርቡን  ብቻ እንኳ ብናይ በደርግ ዘመነ መንግሥት በቅትታ የቤተ ክርስቲያኒቱን  እንቅስቃሴ የሚከታተል ከመንግስት ሥራ አስኪያጅ እየተመደበ የቆየ ቢሆንም ከደርግ ውድቀት በኋላ ሀገሪቱን በኃይል የተቆጣጠረው የኢህዴግ መንግሥት ደግሞ ከቀድሞ በከፋ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጫናውን ከባድ እንደ አደረገው በለፉት  ዓመታት በግልጽ ታይቷል አሁንም እየታየ ያለ ችግር ነው።ምክንያቱም ቤተክህነቱ የቤተ ክርስቲያኗ ሳይሆን የመንግሥት ተቋም እስኪመስል ድረስ በሰፊው እጁን አስገብቶ በመሥራት ቤተ ክርስቲያኗን ሲያምሳት ቆይቷል ።በዚህም ምክንያት ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይህን ድርጊት  እየተቃወሙ ህይወታቸው አልፏል።
በደርግ ዘመን የነበረው ማእበል በኢህዴግ ዘመን ሞገዱ በርትቶ ከፍ ብሎ ከቤተ ክርስቲያኗ  ጉልላት ላይ በመውጣት እሱ የፈለገውን ፓትርያርክ በማስቀመጥ ቤተ ክርስቲያኗን ደፈረ፤ አባቶችን በመከፋፈል ጣልቃ በመግባት ዓላማው እንዲሳካለት አደረገ፤  ይህም ሊሆን የቻለው ብጹአን አባቶች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለዚች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ህልውና ቅድሚያ በመስጠት  በአንድነት  ሊቆሙ ባለመቻላቸው ነው።




በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይኖት ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ  በቅዱስ ሲኖዶስ ምላዓተ ጉባኤ የተመረጡት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በመልካም ጤንነትና በህይወት እያሉ የመላ ሕዝበ ክርስቲያኑና ካህናቱ ድጋፍ ሳይለያቸው መንበራቸውን በኃይል እንዲለቁ  መደረጉ ሁሉም የሚያውቀው እውነት ነው። እንደተለመደው በፈቃዳቸው ነው የለቀቁት ተብሎ እንዳይዋሽ በወቅቱ ፓትርያርኩን ከስልጣናቸው አስገድደው ያወረዱት ጠቅላይ ሚንሥተር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ፓትርያርኩን ከመንበራቸው አውርደው ለቤተ ክርስቲያኗ መለያየት ምክንያት መሆናቼው እንደሚጸጽታቸው በዓለም መድረክ ላይ ቀርበው የተሠራውን  ስህተት አምነዋል ።
አቶ ታምራት ላይኔን መንፈስቅዱስ አፋቼውን ከፍቶ ፊታቸውን ጸፍቶ ያናገራቸው ጠቢቡ ሰሎሞን  ለሁሉም ጊዜ አለው ባለው መሠረት እውነትና ንጋት እያደር እንደሚባለው የአባቶቻችን አምላክ ይሄን በማድረጉ ሎቱ ስብሐት ብለን  እናመሰግነው አለን።  ምንም እንኳን ያለፈውን ነገር ለታሪክ ባለሟያዎች ብንተወውም ለማስታወስ ያህል መጥቀሱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም አንድ ነገር መዘንጋት የለበትም ። ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ መንበሬን አለቅም ብለው በነበረበት ጊዜ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በአንድነት ከጎናቸው ቁመው ቢሆን ኑሮ  ዛሬ ላለንባት ለቤተ ክርስቲያኗ መከፋፈል ባልተደረሰም ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመራው አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በደነገጉለት ቀኖና ነው። ቀኖና ቤተ ክርስቲያኑ የሚያዘው አንድ ፓትርያርክ በኅይወት እያለ መንበሩን መልቀቅ እንደሌለበት የሚደነግገው አንቀጽ ተጥሶ በሕጋዊው ፓትርያርክ ላይ ህገ ወጡ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ 5ኛ ፓትርያርክ በመባል በመንበሩ ላይ እንዲቀመጡ ተደረገ የወያኔ መንግሥት የፈለገውን ዓላማ ለማሳካት ብሎ  ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጥሶ  ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አፍርሶ  አቡነ ጳውሎስን በቅዱሱ መንበር ላይ ቢያስቀምጣቸውም በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጭ የሚገኝ ሕዝበ ክርስቲን አንድ ቀን አባትነታቸውን ሳያምንባቸው ሃያ ዐመት ሙሉ በተቃውሞና በውግዘት  ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ከሀገር  ውጭ በስደት ሁኖ የቤተክርስቲያንን ሥራ በመሥራት  ላይ ካለው በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋርም ተወጋግዘዋል ውግዘቱም  ሳይፈታ የሰላምና የአንድነት ጉባኤ በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የሽምግልና ሥራ እየሠራ በአለበት በዚህ ጊዜ ፤ምዕመናንና ምዕመናት ሁለቱም ሲኖዶሶች የቤተ ክርስቲያኗን አንድነት ከነገ ዛሬ ያስተካክላሉ ብለው በተስፋ ሲጠብቁ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየተዋል ።ይህም ማኅበረ ካኅናቱን እጅግ ያሳዘነ ዐቢይ ጉዳይ  መሆኑን ሳንገልጽ አናልፍም።ምክንያቱም በሕይወት እያሉ የተበላሸው ተስተካክሎ የተጣሰው ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ተመልሶ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ችግር በእርቀ ሰላም ተፈትቶ ቢሆን ኖሮ  ለሁሉም  ቀላል ይሆን ነበር ።
 ነገርግን ይህ ባለመሆኑ የገባያ ግርግር ለቀጣፊ ይመቸዋል እንደሚባለው ለቤተ ክርስቲያኗ አንድነት ከማሰብ እና ጸሎት ከማድረግ ይልቅ የዚች ቤተ ክርስቲያን ተለያይቶ መቅረት የሚያስደስታቸው በመለያየቷ ምክንያት የላይ ፈሪ የታች ፈሪ በማለት ከሁለቱም ክፍል ፍርፋሪ የሚለቅሙ የውስጥ ጠላቶች በየድህረገጹ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ ሲያናፍሱ በመታየታቸው የቤተክርስቲያን መሥራች የሆነው አምላክ አበው ልብ ይስጣቸው እንላለን።
እስካሁን ቤተ ክርስቲያኗን ለሁለት የከፈለው ጉዳይ በራሱ በእግዚአብሔር ፈቃድ አንደኛው አባት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ስለዚህ አሁን በህይወት ያሉት ቀድሞም ያላግባብ በመንግሥት ኃይል ከሥልጣናቼው እንዲወገዱ የተደረጉት  አባት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደመንበራቼው ሊመለሱ ይገባል። ይህም ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያ የሚገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለቤተ ክርስቲያኗ አንድ መሆን በአድነትና በቅንነት ሲቆሙ ብቻ ነው።
ይህ ካልሆነ ግን ባለፉት ሃያ ዓመታት እንኳ የተለያዩ  ጥናቶች እንዳመለከቱት በቤተ ክርስቲያኗ መከፋፈል ምክንያት ወደ14 ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናን ወደሌላ ቤተ ዕምነት እንደሄዱ ተረጋግጧል።
 ቅዱስ ሲኖዶስ ካለፈው ስህተት ተምሮ ለቤተ ክርስቲያንና ለምዕመናን አንድነት ሲል ቀኖናዉን መልሶ መጠበቅና ማስጠበቅ ይገባዋል እንላለን። ያለፈው ስህተት እናዳይደገም  በታሪካዊቷና ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ የታሪክ ጠባሳ ለትውልዱ እንዳይተላለፍ ፤ትውልዱም በአባቶች ላይ እምነት እንዳያጣ በኢትዮጵያ ያሉ የቅዱስ ሲኖዶስን አባላት በቤተ ክርስቲያን አምላክ እያሳሰብን የሚከተለውን  ያቋም መግለጫ እናስተላልፋለን። 


  1. አሁን በስደት ላይ ያሉት አባት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በስቸኳይ ወደመንበራቸው እንዲመለሱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በፍጹም ፍቅርና አንድነት የተጣለባችሁን መንፈሳዊ ግዴታ በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ እንድታስወግዱ ፤ቤተ ክርስቲያንን እንድትጠብቋት መንፈስ ቅዱስ እናተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው እና ለራሳችሁ ልትጠነቀቁ ይገባል የሚለውን ቃል እንድትፈጽሙና ከታሪክ ተጠያቂነት እንድትድኑ። ይህ ባይሆን ግን በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ከቀድሞ በከፋ ሁኔታ የልዩነት አድማሱ የእየሰፋ እልባት ወደማይገኝለት ችግር እየገባን እንደሆነ ከወዲሁ እንድታውቁ እና እንድታስቡበት እንጠይቃለን፤
  2. በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተጋረጠው ችግር ሳይፈታ ለሹመት የሚሯሯጡትን የቤተ ክርስቲያንና የሀገር ጠላቶች በጽኑ እንቃወማለን፤
  3. የኢትዮጵያ  ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፤ አባቶች ካኅናት፤ዲያቆናት፤የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች መላው ህዝበ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን ቀኖና እደቀድሞው እንዲስተካከል ወደፊትም ተጠብቆ  እንዲኖር በጸሎትም በሀሳብም እድትረባረቡ በቤተ ክርስቲያኗ ስም እንሳስባለን፤
  4. መንግሥት እስካሁን በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የሠራውን ስህተት አርሞ እጁን ከቤተ ክርስቲያኗ ላይ በማንሳት ለቤተ ክርስቲያኗ አንድነት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍና በስደት ያሉት ፓትርያርክ ወደመንበራቸው ተመልሰው መለያየት ተወግዶ ሁሉም ለአንዲት ኢትዮጵ በጋራ እንዲረባረብ እንቃፋት ከመሆን  እንዲታቀብ እንላላን፤
  5. በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካና የኅሊና እሥረኞች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ ከሥር ተፈትተው እንደማንኛውም ኢትዮጵዊ ዜጋ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን በነጻነት  እንዲገልጹ እንጠይቃለን፤
  6. በአሁኑ ሰዓት አገሪቱን እየመራ ያለው መንግሥት ከመቼውም በላይ ለሰላም በመነሳት  እና ከተቀዋሚዎች ጋር በመስማማት ብሔራዊ እርቅ ሁኖ በሁሉም የተቃውሞ ጎራ ያሉት ወገኖች የሚሠሩት  ለሀገርና ለህዝብ እስከሆነ ድረስ እርቀ ሰላም እንዲመሠረቱና ሀገራችንን የሰላም ቀጠና በማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተቻችሎና ተከባብሮ በመኖር አብሮ የመኖር እረዕያችን እውን እንዲሆን ፈቃደኝነትን እንዲያሳዩ ስንል እናሳስባለን።
በመጨረሻም ሁሉን በፈቃዱ ማድረግ የሚቻለው ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያሉትን  የአባቶቻችን አንድነት እንዲያሳየን እንለምነው አለን ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፤
ነሐሴ 26 ቀን 2004 ዓ.ም
ጀርመን ፍራንክፈርት