20111220

የቅዱስ ሚካኤል ስሞች




መላእክት ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ቢሆንም በ99 ነገድ የተከፈሉና አለቆችም ያሏቸው ናቸው፡፡ የእነዚህ ሁሉ መላእክት አለቃ የሆነው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ በትህትናው ልዕልናን ያገኘው ቅዱስ ሚካኤል በእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠው ክብር ከማንኛውም መልአክ የበለጠ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡

ሚካኤል ማለት ‹ከመ እግዚአብሔር እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው; ማለት ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ገናንነትና እሱን የሚመስል አምላክ እንደሌለ የሚያመለክት ነው እንደ እግዚአብሔር ያለ ቅዱስ ንጹሕ ርህሩህ ኃይል ረቂቅ ማነው መልሱ የለም ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል የስሙ ዘርፍ ሆነው የሚጨመሩ መጠሪያዎች አሉት እነዚህም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠውን የባለሟልነት ክብር የሚገልጹ ናቸው፡፡ ይኸውም መልአከ ኃይል$ መጋቤ ብሉይ$ መልአከ ምክሩ…ናቸው፡፡ መልአከ ኃይል የተባለው እግዚአብሔር በሱ አማካይነት ታላላቅ ሥራዎችን በመሥራት ኃይሉን ስለገለጸ$ ዲያብሎስን ከነሠራዊቱ ስላሸነፈ ነው፡፡ መጋቤ ብሉይ የተባለበት ምክንያት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከእግዚአብሔር እየተላከ ብዙ ታላላቅ ሥራዎችን የሠራ በመሆኑ ነው፡፡

መልአከ ምክር ወይም የእግዚአብሔር የምክሩ አበጋዝ የተባለበት ምክንያት እግዚአብሔርን በምክሩ ይረዳዋል ለማለት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ ለወዳጁ ለቅዱስ ሚካኤል ይገልጽለታል በሱም አማካኝነት ይሠራል ለማለት ነው፡፡

ቅዱስ ሚካኤል በመጽሐፍ ቅዱስ

ቅዱስ ሚካኤል በዚህ ሁሉ ልዕልና ላይ ትሕትናን ደርቦ የያዘ በጸሎቱ ተማጽኖ በተራዳኢነት አምኖ ለሚለምነው ሁሉ ፈጥኖ በመድረስ ከሠራዊተ አጋንንት ተንኰል የሚያድን መልአክ ነው፡፡ ወደ ቅዱስ መጽሐፍ ስንገባ ለቅዱስ ሚካኤል የተሰጠውን ክብርና ባለሟልነት እንዲሁም የሠራቸውን ሥራዎች እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ (ኢያሱ 5$13-15) እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹እንዲህም ሆነ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፡፡ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፡፡ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን አለው፡፡ እርሱም አይደለሁም እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቻለሁ አለ፡፡ ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደ፡፡ ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድን ነው አለው፡፡ የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን አንተ የቆምህበት ሥፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው፡፡ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ ይላል፡፡ ይህን ጥቅስ ልብ ብለን ብናጤነው ለሌላው ሁሉ መርህ ይሆናልና ጥቂት ለማብራራት እንሞክራለን፡፡

እንዲሁም እግዚአብሔር ራሱ ለኢያሱ ‹‹…በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም ከሙሴ ጋር እንደሆነው እንዲሁ ካንተ ጋር እሆናለሁ አልጥልህም አልተውህም፡፡…›› (ኢያሱ 1$1-9) በማለት ምን ያህል እንዳከበረው ያስረዳል፡፡ እስራኤላውያን አሞራውያንን በወጉ ጊዜ ቀኑ ስለመሸባቸው ከመደበኛው የተፈጥሮ ሕግ ውጭ ቀኑ እንደማይጨልምና መዓልቱ እንዲረዝም ኢያሱ በጸሎት ፈጣሪውን ስለጠየቀ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ቀኑን አስረዝሞ ከሰማይ በረድ አዝንሞ ጠላቶቻቸውን በማጥፋት የፈጸመውን አስደናቂ ተአምር እንዲህ ብሎ ጸፏል፡፡

‹‹...ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል (ልመና) የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም›› (ኢያ 10$12-14) በማለት ተገልጿል፡፡ በጠቅላላው ከኢያሪኮ ጀምሮ ታላላቅ የአሕዛብ ምሽጐችን አፍርሶ አሕዛብን አጥፍቶ እግዚአብሔር ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብ የማለላቸውን የተስፋይቱን ምድር ለልጆቻቸው ያወረሰ ኢያሱ ነው፡፡

ይህ የእስራኤል መሪ በእጅ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ የተገለጸለት ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን አላወቀም፡፡ ከቃሉ እንደምንረዳው ከራሱ ወገን ወይም ከጠላቶቹ ወገን የሆነ አንድ ወታደር መስሎት ነበር፡፡ መልአኩ በሰው አምሳል ስለተገለጸለት አላወቀውም ነበር፡፡ ያነጋገረውም ያለ ፍርሃት ያለ ጭንቀት ያለድንጋጤ ወታደሮቹን እንደሚያነጋግር ዘና ብሎ ነው፡፡ ሆኖም ከመልአኩ የተሰጠው መልስ ታላቅ መሪና ነቢይ የሆነውን የኢያሱን አስተሳሰብ ለወጠው፡፡ ይኸውም ‹‹ከወገኖችህ ወይም ከጠላቶችህ አይደለሁም እኔ አሁን መጥቻለሁ$ የሚለውን ቃል ሲሰማ ኢያሱ በፊቱ የቆመው ተራ ወታደር ሳይሆን የመላእክት ሠራዊት አለቃ ከሙሴ ሳይለይ የእስራኤልን ሕዝብ የሚጠብቅ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን ሲረዳ ለመልአኩ ክብር መስጠት ስለሚገባ የአክብሮት ስግደት ሰገደለት›› #ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድነው;$ በማለት በትህትና ጠየቀ፡፡ ጌታዬ አንተ ቅዱስ ሚካኤል ለኔ ለባሪያህ ለኢያሱ የምትነግረኝ ምንድነው; በማለቱ የእግዚአብሔርን ክብር ለፍጡር መስጠቱ አይደለም መላእክት ጌቶች ይባላሉ፡፡ ጌትነታቸውም የጸጋ ጌትነት ነው፡፡

ኢያሱ መልአኩን ጌታዬ ብሎ ከጠራው እኛማ ኃጢአተኞች ጌታዬ፤ ቀዱስ ሚካኤል ለኔ ለባሪያህ ጸልይልኝ መጥተህ አድነኝ…በማለት የአክብሮት (የጸጋ) ስግደት በመስገድ ብንለምነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውጭ አልወጣንም፡፡ የፈጣሪን ክብር ለፍጡር አልሰጠንም፡፡ ተሳስታችኋል የሚለን ሰው ቢኖር እኛ አብነት ያደረግነው የእግዚአብሔር ወዳጅ ኢያሱን ስለሆነ ኢያሱም ተሳስተሃል ይባል፡፡ መልአኩም ኢያሱ ያቀረበለትን የአክብሮት ስግደትና ጥያቄ በመቀበል ከእግዚአብሔር የተሰጠውን መልእክት ነገረው፡፡ ኢያሱም ትእዛዙን ፈጸመ፡፡

እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ማለት መላእክትን ፈጥሮ የሚገዛ፣ የሚያዛቸው፣ የሚቀድሳቸው ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ የሚለው ከፈጣሪ በታች በመላእክት ላይ በፈጣሪ የተሾመ ማለት ነው፡፡ መላእክት አለቆቻቸውን ያከብራሉ፤ ለእነሱም ይታዘዛሉ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት ሁሉ አለቃ ስለሆነ ከትእዛዙ አይወጡም፤ ሠራዊተ መላእክት የሚያከብሩትንና የሚታዘዙለትን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን እኛም እንደ ኢያሱ እናከብረዋለን እንታዘዘዋለን፡፡ መላእክትን ማክበርና መታዘዝ እንደሚገባ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡፡ #በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክህን በፊትህ እሰዳለሁ፤ በፊቱ ተጠንቀቁ፤ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት፤ አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፣ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፣ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፣ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ፣ መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና…$(ዘጸ.23$2ዐ-22) በማለት ለሙሴ ተናግ ል፡፡ ይህ ቃል ለአንድ ጊዜ ብቻ ለሙሴና ለሕዝቡ ተነግሮ ያበቃ ሳይሆን እስከዛሬና ወደፊትም የሚቀጥል ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ያን ጊዜ ሕዝበ እስራኤልን ፊት ፊት እየመራ ጠላቶቻቸው አሕዛብን አጥፍቶ ምድረ ርስትን ምድራዊት ኢየሩሳሌምን እንዳወረሳቸው ዛሬም ይኸው መልአክ ቅዱስ ማካኤል እስራኤል ዘነፍስ የተባልን ህዝበ ክርስቲያንን ፊት ፊት እየመራ ጠላቶቻችን ሠራዋተ አጋንንትን እያጠፋ ምድረ ርስት ወደተባለች ሰማየ ሰማያት ያገባናል፡፡ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ለአዲስ ኪዳን ሕዝብ ምሳሌ ስለሆነ በታሪክነቱ ብቻ ተነግሮ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ኦሪት ሰም ሲሆን ሐዲስ ኪዳን ደግሞ ወርቅ ነውና፡፡

ይህ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ያወጣ፣ በበረሃ 4ዐ ዓመት የመራቸው፣ ምድር ርስትን ያወረሳቸው መሆኑን በሌላ ስፍራ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹…በእስራኤል ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፊቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፡፡›› (ዘጸ.14$15-20) በዚህ መሠረት እስራኤልን ይመራ የነበረው የእዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ እንዲሁም በኮሬብ ተራራ እግዚአብሔር ለሙሴ ሐመልማል ከነበልባል ተዋሕዶ በተገለጸለት ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አልተለየም ነበር፡፡ (ዘጸ.3$1-6፣ የሐዋ. 7$3ዐ-34) በኦሪት የእግዚአብሔር መልአክ እየተባለ የሚጠራው አብዛኛውን ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ በድርሳነ ሚካኤልም ተጽፎ ይገኛል፡፡ (መዝ.33$7) ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ (ቅዱስ ሚካኤል) እግዚአብሔርን በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸዋል (በኢሳ.37$36) ›› የእግዚአብሔር መልአክ(ቅዱስ ሚካኤል) መጣ፡፡ ከአሞራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ…›› በማለት ቅዱስ ሚካኤል ሕዝቅያስን እንዴት እንዳዳነው ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ሚካኤል ያልረዳው ቅዱስ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በዳን.1ዐ$13 ‹‹የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ$ በማለት የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ተገልጿል /ዳን.1ዐ$21/፡፡ በዚሁ በትንቢተ ዳንኤል ም.12$1 ላይ ‹‹በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል በማለት ታላቅነቱን፤ለሰው ልጆች ሁሉ በአማላጅነቱና በተራዳኢነት የሚቆም እንደሆነ በማያሻማ ቃል ተገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ ዲያብሎስ ከነሠራዊቱ በእግዚአብሔር ላይ ባመፀ ጊዜ ከክብሩ ያዋረደው ወደምድር የጣለው ቅዱስ ሚካኤል ቅዱሳን መላእክትን በመምራት ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ ጋር ስላደረገው ጦርነትና ስለተቀዳጀው ድል ቅዱስ ዮሐንስ እንዲሀ በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ፤ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፡፡ አልቻላቸውምም፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም፡፡ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው፡፡ ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀድሞው እባብ ወደ ምድር ተጣለ፡፡ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ…$ (ራእ.12$7-9) ዛሬም ቅዱስ ሚካኤል ሰዳዴ አጋንት አጋንንትን የሚያሳድድ በመሆኑ ከሰይጣንና ከሠራዊቱ መከራ እንዲያድናቸው በጸሎት ለሚለምኑት በቃል ኪዳኑ ለሚማፀኑት ሁሉ ፈጥኖ እየደረሰ ይታደጋቸዋል፡፡ በዙሪያቸው እየከተመ አጥር ቅጥር ሆኖ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድናቸዋል (መዝ.33$7)፡፡

በመልእክተ ይሁዳ ቁ.9 ‹‹የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገስጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም$ በማለት ቅዱስ ሚካአል ዲያበሎስን እንኳ እግዚአብሔር ይፍረድብህ ከማለት በቀር ሌላ ቃል አለመናገሩ ታጋሽነቱን ያሳያል፡፡

የቅዱስ ሚካኤል ክብር

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቅዱስ ሚካኤል ለማንም ያልተሰጠ እጅግ ታላቅ የሆነ ክብር እንደተሰጠው ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ይኸውም በዕለተ ምጽአት ጌታችን ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ በክበበ ትስብአት በግርማ መለኮት በሚመጣበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሙታን ላይ ሥልጣን የተሰጠው ለዚሁ ለኃያሉ መልአክ ለቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ በሚገባ ገልጾታል፡፡ እነሆ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ ሁላችን አናንቀላፋም፡፡ ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋል፤ ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን ይላል(1ቆሮ.15$51-52) ከዚሁ ጋር በተጨማሪ ‹‹በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና በክርስቶስ የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ…›› (1ተሰ..4$15-16) በማለት በዕለተ ምጽአት ምን ያህል ክብርና ጌትነት እንደሚሰጠው ይገልጽልናል፡፡

የቅዱስ ሚካኤል በዓል

የቤተ ክርስቲያን አባቶች በየወሩ በ12 መታሰቢያውን እንድናደርግ አዘውናል፡፡ ይህንንም ያልቻለ በዓመት አራት ዐበይት በዓላትን ከቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ጀምሮ እንደተቻለ ማዝከር ይገባል፡፡ እነዚህም ኅዳር 12 ቀን ቀጥሎ ሰኔ 12 ቀን ከዚያም ነሐሴ 12 ቀንና ታኅሳስ 12 ቀን ናቸው፡፡ ከሁሉም የሚበልጠው ታላቁ በዓሉ ኅዳር 12 ቀን ነው፡፡ በዚህም ዕለት እግዚአብሔር በሰማይ ካሉ ሁሉ በላይ አድርጐ ሾመው፡፡ ስለትሕትናውና ስለ መታዘዙ ጌታውን ፈጣሪውን የከዳና የበጐ ሥራ ሁሉ ጠላት የሆነውን ሰይጣንን ድል ይነሣ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው፡፡ በዚህ ዕለት እንዲሁ ከላይ እንደተገለጸው ቅዱስ ሚካኤል በታላቅ ክብር ሆኖ በንጉሥ ጭፍራ አምሳል ለነዌ ልጅ ለኢያሱ የታየበት ዕለት ነው፡፡

በቅዳሴያችን ‹‹ተውህቦ ምሕረት ለሚካኤል፤ ለሚካኤል ምሕረት (ይቅርታ ርኀራኄ) ተሰጠው ይላል፡፡ ነቢዩ ሄኖክም ምሕረት ለሚካኤል መሰጠቱን ገልጿል፡፡ ትሕትናውን ታዛዥነቱን አስረድቷል (ሄኖክ. 6 ቁ.5 ምዕ.10 ቁ.12)፡፡

የሰማያውያን ሠራዊት አለቃ ለሰው ሁሉ የሚራራና ስለ ሰው ልጆች ሳያቋርጥ ወደ ፈጣሪው የሚለምን ርኀሩኀ ትሑት የሆነው ኃያሉ ቅዱስ ሚካኤል የሠራውን ሥራ የክብሩን ገናንነት ጽፈን ለመጨረስ ስለማይቻለን በዚሁ እናበቃለን፡፡ ጸሎቱ እና በረከቱ፣ ተራዳኢነቱም ሀገራችንና ሕዝባችንን ይጠብቅልን አሜን፡፡ (ምንጭ ማህበረ ቅዱሳን )

3 comments: