20111221

እንኳን ለአባታችን ኣባ ሳሙኤል የእረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ


እንኳን ለአባታችን ኣባ ሳሙኤል የእረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ አባታችን አባ ሳሙኤል ዘደብረ ዋሊ (ዋልድባ) የተባሉ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ኣባታቸው እስጢፋኖስ እናታቸው ዓመተ ማርያም ይባላሉ:: ትውልዳቸው አክሱም ሽሬ አካባቢ ተወለዱ በኋላም አባታቸውና እናታቸው ስለሞቱባቸው ወደ ገዳም ሄደው ገቡ በዚህም ጊዜ በመንፈሳዊ ትምህርታቸው ላቁ (ጎለመሱ) ተነስተውም ወደ ደብረ መንኮል ገዳም ገቡና ከአባ አድኃኒ ከተባሉ አባት መነኮሱ በዚህም ገዳም ኢይበልዕ ዘእንበለ ሐምል ይለዋል ከጎመን በስተቀር ሌላ ምግብ አይበሉም ነበርና ሲሰግዱም እግራቸው እስኪአብጥ ድረስ ይሰግዱ ነበር። በጾመ ፵ ጊዜም ፵ መአልትና ፵ ሌሊት ምንም ሳይቀምሱ ቆዩ በዚህም ጊዜ ብዙ አናብስት ተሰብስበው ወደ እሳቸው መጡና ግማሾቹም ለእሳቸው እንደፈረስ መሄጃ ግማሾቹም ለቅዱሳን መጻህፍትቶቻቸው መጫኛ እንዲሆኑ የረገጡትን መሬት እየላሱ እንዲኖሩ ታዘዙ። በዚህ ዓይነት ኑሮ ሲኖሩ ወደ ዋልድባ ገዳም ገብተው ገዳሙን አቀኑ መሰረቱ በዋልድባ ገዳም ሲጸልዩ ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ መንበሩን ሲያጥኑ ተገለጸላቸው ከዚህም ሌላ እሳቸው ቅዳሴ ገብተው ቅዳሴ ማርያምን ሲቀድሱም ሆነ ሲደግሙ ከመሬት አንድ ክንድ ከፍ ብለው መሬት ለቀው ይቆሙ ነበር ለእሳቸው ግን አይታወቃቸውም ነበር ከብቃታቸው ብዛት የተነሳ ሌላው ደግሞ ከፍቅራቸው ጽናት የተነሳ ቅዳሴዋንና ውዳሴዋን በቀን በቀን በእድሜዋ ልክ ፷፬ ጊዜ ሲደግሙ ከ፪ ክንድ በላይ ከመሬት ይለቁ ነበር ከሰማይ የወርቅ ጽዋ ወርዶላቸው የቀድሱበት ነበር አባ ሳሙኤል ዋልድባን እንደመሶብ በእጃቸው ይዘው አስባርከዋታል የበረከት ሀገር አንድትሆን ዛሬ በዋልድባ ረሐብ የለም ቅዳሴ ማርያም ሳይደግም የሚውል መነኩሴ የለም አባ ሳሙኤል በዋልድባ ሁነው አባ አንበሳ በአዘሎ ሁነው አባ ብንያም በግብጽ ሁነው ሲጸልዩ በመንፈስ ይተያዩ ነበርና ተቀጣጥረው ፫ቱም በአንበሳ ላይ ተቀምጠው ወደ ምድረ ከብድ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ በረከትን ለማግኘት ሄዱ።አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ እረፍታቸው ታህሣስ፲፪ ቀን ነው ። የአባታችን ያባ ሳሙኤል አምላክ ይጠብቀን ረድኤት በርከታቸው በኛ በልጆቻቸው ላይ ይደርብን አሜን!!!

1 comment: